“እንደ ምክር ቤት አባልነቴ እንደ ታፈንኩ ይሰማኛል”፦ የምክር ቤት አባል ጥያቄ

0
841

ማክሰኞ ኀዳር 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እያካሄደ ነው፡፡

በዚህም መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፓርላማው ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፦

በተለያየ ጊዜ በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው ማብራርያ ሲሰጡ ለፓርላማ አባላት በግልጽ የሚነገር መልእክት አለመኖሩ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አንድ የምክር ቤቱ አባል ተናግረዋል፡፡

አፈ ጉባኤው ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ማብራርያ ሊያመሩ ሲሉ በመሀል ገብተው የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ለማቅረብ እድል የወሰዱት የምክር ቤት አባሏ በምክር ቤቱ አሠራር ላይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በዋናነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ቀርበው ለተወካዮቹ ጥያቄ ማብርሪያ እንደሚሰጡ በግልጽ የሚነገር አለመሆኑ፣ ይልቁንም ጉዳዩ በብልጽግና ፓርቲ ቴሌግራም ገጽ ብቻ የሚለቀቅ መሆኑና መደበኛ በሆነ መንገድ አለመነገሩ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የማቅረብ እድልም ለሁሉም በፍትሐዊነት እኩል የሚሰጥ አለመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባሏ እንደ ምክር ቤት አባልነቴ የወከልኳትን የአዲስ አበባን ጥያቄ ለማቅረብ እንደ ታፈንኩ ይሰማኛል ብለዋል፡፡ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የምክር ቤት አባሏ ጥያቄያቸውን በዛው እንዲያቀርቡ እድል ሰጥተዋል፡፡ የምክር ቤት አባሏ አዲስ አበባ ከተማ ከምርጫ 97 በኋላ ለብዙ ችግሮች መዳረጓንና የፖለቲካ ማንነት ቀውስ ገጥሟታል ሲሉ ሦስት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም፦

👉የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚው ያለበት ደረጃን እና የኢንቨስትመንት ጉዳይን በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጥ፣

👉የሰላም ስምምነቱ ሂደት አንደምታውና ፋይዳው ምንድነው?

👉ስምምነቱን ፈጥኖ ተግባራዊ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል?

👉በጦርነቱ የተጐዱ አካባቢዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የመልሶ ለመገንባት ምን ዝግጅት ተደርጓል?

👉የአሸባሪው የኦነግ ሸኔ የትጥቅ ምንጭ ምንድን ነው?

👉በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ እና በቡድኑ ላይ ዘመቻ ሲወሰድ እንዲከሽፍ የሚያደርጉ ኃላፊዎች እንዴት ይታያሉ?

👉መንግስት የኦነግ ሸኔን ጉዳይ በሰሜን ኢትዮጵያ በወሰደው እርምጃ መሰረት ለመፍታት ያስባል ወይስ በጦር?

👉 የክልል ልዩ ሀይሎች እስከ ታጠቁት ጦር መሳሪያ ከአማፂያን ጋር እየተቀላቀሉ መገኘታቸውን ተከትሎ ኹሉም የክልል ልዩ ሀይሎች ፈርሰው መከላከያን እንዲቀላቀሉ ጥያቄ ቀርቧል።

👉 እንዲሁም የልማት ተቋማትና መሰረተ ልማቶች ይሰራልን፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ግለሰቦችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ከም/ቤቱ አባላት ተነስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here