በአንድ ዓመት ውስጥ ከ50 በላይ ሹፌሮች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ

0
1239

በአንድ ዓመት ውስጥ ከ50 በላይ ሹፌሮች በታጣቂዎች መገደላቸውን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በአንድ ዓመት ውስጥ ከ50 በላይ ሹፌሮች በታጣቂዎች መገደላቸውን ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ጸሐፊ ሰጡ ብርሃን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር በአገር ዐቀፍ ደረጃ በማተኮር የሹፌሮችን መብት ለማስጠበቅ በባህር ዳር ከተማ የተቋቋመ ማኅበር ሲሆን፤ በሹፌሮች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና እገታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታውቋል።

ማኅበሩ ባሰባሰበው መረጃ፣ ከጥቅምት 2014 እስከ ጥቅምት 2015 ድረስ ከ50 የሚበልጡ ሹፌሮች መንገድ ላይ ታግደው ከታጣቂዎች በሚተኮስ በጥይት ተገድለዋል ብሏል። ማኅበሩ “ወንበዴዎች” የሚላቸው አካላት የሚያደርሱት የግድያ እና እገታ ጥቃት ሊቆም ባለመቻሉ ከዚህ በፊት ሹፌሮች ሥራ አቁመው መብታቸውን ለማስጠበቅ ባደረጉት ሙከራ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር እንዳይቆሙ በደብዳቤ ጭምር ሲያስፈራራቸው እንደነበር ሰጡ አስታውሰዋል። ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲቆም ነው ወይስ የሹፌሮች እስትንፋስ ሲቆም ጩኸቱን የሚያሰማው?›› ሲሉም ጠይቀዋል።

ሰጡ አክለውም፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሹፌሮች የሥራ ማቆም አድማ እንዳያደርጉ ውሳኔ ባስተላለፈ በኹለት ወር ውስጥ ከ10 በላይ ሹፌሮች ሲገደሉ፤ በጉዳዩ ዙሪያ እንኳ ጥቃቱን የሚያወግዝ መግለጫ አለማውጣቱ  ሹፌሮችን ያስቆጣ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የጅቡቲን ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ሹፌሮች በሦስት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ መድረስ ግዴታቸው ስለመሆኑና በተወሰነው ቀን ውስጥ ካልደረሱ ከአምስት ሺሕ ብር ጀምሮ በየቀኑ የሚቀሡ ሲሆን፤ በታጣቂዎች ታግተው ሲገደሉና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሲጠየቁ ግን የሚደርስላቸው የመንግሥት አካል አለመኖሩ መንግሥት የሹፌሮች ሕይወት እንደማያሳስበው ግልጽ ማሳያ ነው ሲል ማኅበሩ ትችትም ሰንዝሯል።

ቀደም ሲል ታጣቂዎች በሹፌሮች ላይ በብዛት ጥቃት ሲያደርሱ የነበረው ሌሊት ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ጥቃቱ በቀንም እየተከናወነ መሆኑን ጸሐፊው ተናግረዋል። የታጠቁ ኃይሎች በሹፌሮች ላይ ጥቃት የሚያደርሱት በማናለብኝነት ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

ጥቃቱ በብዛት የሚደርሰው በአፋር ክልል ከሚሌ አዋሽ አርባ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች፤ በአማራ ክልል ከጎንደር አብርሃ ጅራ እስከ ሾዲህ፤ በደብረ ታቦር እና ሌሎች አካባቢዎች፤  በኦሮሚያ ክልል በፍቼ ጎሃጽዮን እና ወለጋ በኩል በኹሉም ቦታዎች፤ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ነው ተብሏል።

ሹፌሮች በየወቅቱ በታጣቂዎች እየተገደሉ መሆኑን ተከትሎ ሥራ አቁመው መብታቸውን የማስጠበቅ አድማ ለማድረግ ያቀዱ ሹፌሮች እንዳሉም ተጠቅሷል። ታጣቂዎች ካሁን በፊት ሹፌሮችን በየመንገዱ እያገቱ እስከ 700 ሺሕ ብር እንደሚጠይቁ ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ታጋቾች እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየተጠየቁ መሆናቸውን ሰጡ ጠቁመዋል።

በተለይም ወደ ነገሌ ቦረና መንገድ ልዩ ሥሙ ገርብቾ በሚባል አካባቢ በሹፌሮች ላይ የሚደርሰው ዘረፋ እየተባባሰ መምጣቱም ተገልጿል። ባሳለፍነው ጥቅምት 30/2015 በገርባ ጉራቻ እና ጎሃጽዮን መካከል ቱሉ ሚልኪ በሚባል ቦታ ላይ አንድ ተሽከርካሪ ከእነተሳፋሪዎች እና አንድ ተሽከርካሪ ከእነ ረዳቱና ሹፌሩ በታጣቂዎች መታገታቸው ተሰምቷል።

ከሰሞኑ ከሞጆ ዝዋይ ባለው መንገድ እየተጓዘ በነበረ ተሽከርካሪ ታጣቂዎች በተኮሱት ጥይት ኹለት ወጣት እህትና ወንድም እንደሞቱ እና አራት ተሽከርካሪዎች እንደተቃጠሉ ሰጡ ለአዲስ ማለዳ  አስታውሰዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here