በአዲስ አበባ 50 ሴት ተማሪዎች ከክትባት በኋላ ራሳቸውን መሳታቸው አነጋጋሪ ሆኗል

0
386

በአዲስ አበባ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ብርሃን እና ሰላም ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሃሙስ ጥቅምት 13 እድሜአቸው 14 አመት የሆናቸው የማህጸን ጫፍ ካንሰር ክትባት የወሰዱ አርባ የሚጠጉ ተማሪዎች ራሳቸውን መሳታቸውን ተከትሎ ክትባቱ በክፍለ ከተማው ቆሞ ምርመራዎች መደረግ ተጀምረዋል።

በክፍለ ከተማው ባሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ቁጥራቸው ዝቅተኛ ቢሆንም የተወሰኑ ተማሪዎች በተመሳሳይ ራሳቸውን ስተው ወደ ህክምና መሄዳቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

የክፍለ ከተማው የትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብሩክ ተክለማሪያም እንደሚሉት ሁሉም ራሳቸውን የሳቱት ሴት ተማሪዎቸች በመሆናቸው ምክኒያት ምንአልባት ከክትባቱ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የሚል ጥርጣሬ ይፈጠር እንጂ ከታመሙት ተማሪዎች ውስጥ ክትባት ያልወሰዱ እንደሚገኙ እና ከ 9 እስከ 14 አመት እድሜ ያላቸው ተማሪዎችላይ ተመሳሳይ ስሜት መታቱን ተናግረዋል። በወቅቱም ወደ ወረዳ ሶስት ጤና ጣቢያ ተወስደው ህክምና ያገኙ ሲሆን በተለይም የድካም ስሜት ይሰማናል የሚል ተመሳሳይ ምልክት በመነገራቸው ድካማቸውን የሚያስለቅ ህክምና እግኝተው ከጤና ጣቢያው መውጣታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ሁኔታውን ክትባቱን ለሚያቀርበው የአለም የጤና ድርጅት እንዲሁም ለከተማው ማህበራዊ ጤና አደጋ ክላስተር አሳውቀን ክትባቱ ቆሞ መድሃኒቱ ላይ ምርመራ ተደርጓል›› ያሉት ሃላፊው ‹‹ነገር ግን በአዲስ አበባ የተሰራጨው መድሃኒት ተመሳሳይ የምርት መለያ ቁጥር፣ የመገልገያ ግዜው ያላላፈ እና አያያዙም ላይ ምን ልዩነት አልነበረውም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አንዲት ተማሪ ሀሙስ ከሰአት ራሷን ስታ መውደቋን እና ግዜውም የልጆች መለቀቂያ በመሆኑ ወላጆች እንዲሁም ተማሪዎች መረበሻቸውን ብሩክ ይናገራሉ። ጉዳዩ ድንጋጤ (ፓኒክ) እንድሆነ ድምዳሜ ላይ ለመደረሱ አንዱ ምክኒያት ነው ብለው ሃለፊው የሚጠቅሱትም ይህቺን ራሷን የሳተች ልጅ ይዘው ሆስፒታል የደረሱ ተማሪወችም በየተራ ራሳቸውን እየሳቱ መውደቃቸው እና ክትባቱን ያልወሰዱትም ተመሳሳይ ስሜት ማሳየታቸው መሆኑን ይነገራሉ። ክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ካለው በ 15 ደቂቃዎች ውስጥ የሚያሳይ ሲሆን ተማሪዎቹ የወደቁት ግን ከ አንድ ቀን በኋለ መሆኑ በርግጥም ድንጋጤ በመሆኑ ክትባቱ ከቆመባቸው ምክኒያቶች መካከልም ተማሪዎች እንዲረጋጉ መሆኑን አክለዋል።

የክፍለ ከተማው የጤና ቢሮ ሃላፊ እዮብ ዘለቀ እንደሚሉት ተመሪዎች ክትባቱን ከመውሰዳቸው በፊት የህክምና ታሪካቸው እንደሚወሰድ እና በከተማ ደረጃ እየተሰራ ባለው ዘመቻም በክትባት ላይ ልምድ ባላቸው ባሞያዎች በመሰጠቱ በቂ ቅድመ ትንቃቄዎች መድረጋቸውን ተናግረዋል። በተለይም ተማሪወች ከቤተሰብ ፈቃድ አግኝተው በፈቃደኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የተሰጠ ክትባት እንደሆነ ገልፀው ከክትባቱ በፊት ግን ምርመራዎች እንደማይደረግ ተናግረዋል። ምግብን በተመለከተም የትምህርት ቤት ምገባን ተከትሎ ሁሉም ተማሪዎች ተመግበዋል ተብሎ ግምት መወሰዱን አስረድተዋል።

‹‹ለአዋቂዎች ክትባቱ ሲሰጥ ቅድመ ምርመራዎች ይደረጋሉ፣ ለታዳጊዎች ግን የእድሜ ክልሉ 14 እንዲሆን የተደረገውም የግብረ ስጋ ግንኙነት ይጀምራሉ ተብሎ ስለማይገመት እና ጥናቶችም የሚያረጋግጡት ይሄንን ስለሆነ ለማህጸን ጫፍ ካንሰር ከከትባቱ በፊት ይጋለጣሉ ተብሎ አይገመትም›› ሲሉ ቅድመ ምርመራዎች እንደማይካሄዱ ጠቁመዋል።

የጤና ቢሮ ሃላፊው እንደሚሉትም የእቅዳቸውን መቶ በመቶ ማሳካታቸውን ገልጸው ባሳለፍነው ሳምንትም ተማሪዎችን በየክፍላቸው በመሄድ የማረጋጋት ስራ በመስራት እንዲሁም ከክፍል በመቅረት እና በተለያዩ ምክኒያቶች ያልተከተቡ ካሉ የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ከወላጆች፣ ከህክምና ባለሞያዎች እና ከመምህራን እንዳረጋገጠችው የጤና እክል አጋጥሟቸው የነበሩ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል። ክትባቱ በክፍለ ከተማው ባሉ 10 ወረዳዎች እና 40 ትምህርት ቤቶች የተሰጠ ሲሆን በሌሎች ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ ችግር እንዳልታየ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here