በደቡብ ክልል የ11 ሆስፒታሎች ግንባታ ውል ተቋረጠ

0
878

በደቡብ ክልል በ2009 የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ወቅት ውል ተፈጽሞ ወደ ግንባታ ሒደት ገብተው ከነበሩ ሆስፒታሎች መካከል የአስራ አንዱን ውል ማቋረጡን የክልሉ የጤና ቢሮ አስታወቀ።

በወቅቱ ስድስት መቶ ሠላሳ አራት ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚያወጡ ተገምቶ በጨረታ ለገንቢዎች የተላለፉት ሆስፒታሎቹ፣ በአንድ ዓመት ተኩል ይጠናቀቃሉ ቢባልም በተለይም ከወሰን ማስከበር ችግሮች፣ ከተቋራጮች አቅም ማነስ እንዲሁም በዋናነት የብር ዋጋ ከዋና ዋና የውጪ ገንዘቦች ጋር ሲነፃፀር በመውረዱ ግንባታዎች መጓተታቸው እንደምክንያት ተጠቅሷል።

እያንዳንዳቸው 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጡ የሚገመቱት ሆስፒታሎቹ፣ ዋጋቸው ሦስት እጥፍ በማደጉ የጤና ቢሮው እና ገንቢዎቹ ግንባታው እንዲቆም ማስገደዱን የደቡብ ክልል የሆስፒታሎች ግንባታ አስተባባሪ ኢንጅነር ሳሙኤል ሻሪፎ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

‹‹ከብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የዋጋ ንረት በተፈለገው ፍጥነት ግንባታውን ማካሔድ አለመቻሉ ውል እንድናቋርጥ አስገድዶናል›› ብለዋል። ‹‹ግንባታቸው ከተጀመረ 21 ሆስፒታሎች ውስጥ ማጠናቀቅ የተቻለው በጉራጌ ዞን አገና ሆስፒታልና ወላይታ ዞን ገሱባ የሚገኙ የህክምና መስጫ ተቋማትን ብቻ ነው››።

ውል ሲቋረጥ ነባሩ ኮንትራክተር፤ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ የክልሉ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፤ ከጤና ቢሮ እንዲሁም ከዞን የሚመለከታቸው አካላት በግንባታ ስፍራው ኦዲት በማሠራት ከውለታ አንጻር ምን ያህል እንደተሠራ በመመልከት በክፍያ ሰርተፊኬት የሚፈጸም እንደሚሆን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።
የውል ማቋረጥ ሥራ ሲከናወን ከጥራት በታች የተከናወኑ ሥራዎች እንደተሠሩ የማይቆጠር ሲሆን ቅድመ ክፍያዎችን ኮንስትራክሽን ድርጅቱ እንዲመልስ ይደረጋል ሲሉ ሳሙኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ጀምሮ በኹለት ሳምንታት ውስጥ በኹለት ቡድን በግንባታ ስፍራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ተደርጎ ነባር የሥራ ተቋራጮች የቀራቸውን ሥራዎች እንደሚለቅሙ እና በማረጋገጫ ጭምር በመያዝ የጨረታ ሰነድ የማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዳሉ የሥራ ኀላፊው ተናግረዋል።

ተጫራቾች የጨረታ ሂደቶችን አሸንፈው ወደ ሥራ እንደገቡ የዋጋ ንረት መከሰቱን ማረጋገጣቸውን በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ልማት፤ ዕቅድ እና ኢኮኖሚ አስተዳደር ኀላፊ ፍስሐ ለዕመንጎ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት እንደገና ጨረታ ማውጣት እንደሚያስፈልግ በሕግ የሚፈቀድ አና የተለመደ አሰራር በመሆኑ ስለሚያስገድድ እንደሆነ አቶ ፍስሐ ለኢዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

‹‹ክልሉ ካስጀመራቸው ሃያ አንድ ሆስፒታሎች ውስጥ ኹለቱን መረከቡን በመግለጽ ስምንት ሆስፒታሎች ዝቀተኛ አፈጻጸም ቢያገኙም እያስታመምኩኝ እገኛለሁ፣ ከተቀሩት አስራ ኹለቱ ጋር ያለኝን የግንኙነት ውል ግን ለማቋረጥ ተገድጃለሁኝ›› ሲል ቢሮው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ከ21ዱ ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው እና በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ በ2010 የተጀመረው የአላባ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ፣ በተባለው ጊዜ ማካሔድ ባለመቻሉ የጨረታ ሂደቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል። በ2011 መጀመሪያ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ የሆስፒታል ማስፋፊያ፣ አላባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃ ማደግን ተከትሎ የሚደረግ የማስፋፊያ ሂደት ነበር።

ማስፋፊያው የእናቶች ሥነ-ተዋልዶ፤ የቤተሰብ ምጣኔ፤ የቲቢ ና ሳምባ ነቀርሳ እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ያካተተ ነበር። ሆስፒታሉ በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጣቸውን 13 አገልግሎቶች በማሻሻልና በመጨመር ወደ 19 ማሳደግ እንደሚያስችለውም ታስቦ ሥራው መጀመሩን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ሱሌማን ጊርሚሶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹አሁን ባለበት ደረጃ ሆስፒታሉ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃን ማግኘት የቻለበትን አገልገሎት እየሰጠ ቢገኝም ለህክምና አሰጣጡ አጋዥ የሆኑ ስፍራዎችን ግን ማግኘት አላስቻለውም›› እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ። ‹‹ሆስፒታሉ በቀን 2 መቶ ታካሚዎች የሚያስተናግድ ሲሆን ሀላባን ጨምሮ ከስልጤ ዞን፤ ከሳንኩራ፤ ከከንባታ፤ ከሀዲያ (ሾኔ) እንዲሁም ከኦሮሚያ አርሲ አካባቢ ታካሚዎች የሚያስተናግዱት የህክምና ማዕከል ነው።›› ብለዋል።

ሆኖም ለክልሉ ጤና ቢሮ ግንባታውን በተደጋጋሚ እንዲከናወን ቢጠየቅም ውል እንደተሰረዘና ከዛ ወዲህ ምንም ዓይነት ምላሾች እንዳልተሰጠ ሱሌማን ተናግረዋል። ይህም ፍላጎቱን የሚመጥን አገልግሎት እንዳይሰጥ እንዳደረገው ገልፀዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ ከኻያ አንዱ ጤና ተቋማት በተጨማሪ ሃላባ ወረዳ ሃላባና ጎፋ ዞን ሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ሰባ ሚሊዮን ብር የሚገመት ማስፋፊያ ውል እንዳቋረጠ በመግለጽ በቀጣይ በጨረታ እንደሚሰጥ ተገልጿል። የክልሉ ኮንስትራክሽን ግብአት የዋጋው ከሚገባው በላይ መናር፣ ሥራዎችን መስራት እንዳይቻል እያደረገ በመሆኑ መንግሥት እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here