ሰባት የአፍሪካ አገራት ተመሳሳይ መገበያያ ገንዘብ ሊጠቀሙ ነው

0
2411

የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል የሆኑ ሰባት አገራት በአንድ አይነት ገንዘብ ለመጠቀም ዝግጅቶችን ማድረግ እንጀመሩ አስታወቁ፡፡
ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎንና ደቡብ ሱዳንን ያቀፈው East African Community በመባል የሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ፣ አባል አገራቱ እ.አ.አ ከ2026 ጀምሮ አንድ አይነት የመገበያያ ገንዘብ መጠቀም እደሚጀምሩ አስታውቋል፡፡

ይህን ውጥን ለማሳካትም የምስራቅ አፍሪካ የገንዘብ ተቋም ወይም የምስራቅ አፍሪካ ማዕከላዊ ባንክ የተሰኘ የገንዘብ ተቋም በ12 ወራት ውስጥ እንደሚመሰረትም የማኅበረሰቡ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ፒተር ማቱኪ አስታውቀዋል፡፡

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ይመሰረታል የተባለው ይህ ተቋምም የአባል አገራትን የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎች ለማጣጣም በሚያስችል ሁኔታ ላይ ይሠራል ተብሏል፡፡ አገራቱ በሦስት አመታት ውስጥም የጋራ መገበያያ ገንዘብ እንዲኖራቸው ይደረጋል ያሉት ዋና ጸሐፊው የተቋሙ መቀመጫ የት ይሁን የሚለውን የማኅበረሰቡ የሚኒሰትሮች ምክር ቤት ይወስናል ብለዋል፡፡

በቀጠናው አንድ አይነት ገንዘብን ለመገበያያነት መጠቀም የሰዎችን የንግድ እንቅስቃሴ ያሳልጣል የተባለ ሲሆን፣ የማኅበረሰቡ አላማም በአገራቱ መካከል የጋራ ገበያን መፍጠር እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የማኅበረሰቡ አባል አገራት ድምር ከ300 ሚሊዮን እንደሚበልጥ የተነገረ ሲሆን፣ አንድ ዓይነት ገንዘብ ተጠቃሚ መሆናቸው አለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን የሚስብ መልካም አጋጣሚ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

በአገራቱ መሪዎች መካከል በተደረጉ ከፍተኛ ውይይቶች በመካከላቸው ያለውን የንግድ ልውውጥ የሚያደናቅፉ ከታሪፍ ውጪ የሆኑ፣ በርካታ እገዳዎችን ለማስወገድ ተስማምተዋል ያሉት ዋና ጸሐፊው ይህም በቀጠናው ያለውን የንግድ ልውውጥ አሳድጎታል ማለታቸውን ዘ-ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ እ.አ.አ በ1967 የተመሰረተ ሰባት አባል አገራት ያሉትና ዋና መቀመጫውን በታንዛኒያ አሩሻ ያደረገ ክልላዊ የመንግስታት ድርጅት ነው፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here