የሽግግር ፍትሕና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የመካስ መብት ከኢትዮጵያ ሁኔታ አንጻር

0
875

በሽግግር ፍትሕ ጊዜ ከሚኖሩና ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ የተጎጂዎች የመካስ መብት ነው። የካሳ ጉዳይ ሲነሳም በርካታ ሊሟሉ የሚገባቸው ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው። ሽመላሽ ወንዳለ ይህን ጉዳይ በማንሳት፤ ሊሟሉ የሚገባቸውና የተለመዱ ናቸው የሚባሉት የካሳ ዓይነቶች ዘርዝረዋል። እንዲሁም በጠቅላላው የሽግግር ፍትሕና የመካስ መብትን ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር አስቃኝተዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ማለት አንዲት አገር ወይም አንድ ሕዝብ ከጨቋኝ ሥርዓት ወደ ተሻለ ለማለፍ ወይም ከግጭትና ቀውስ ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሻገር ወይም በእርስበርስ ግጭት ምክንያት ከደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የተለያዩ ጉዳቶች በኋላ ዘላቂ ሰላምና እርቅ በመፍጠር የአገርን የወደፊት እጣ ፈንታ ለማስተካከል የሚታለፍበት የፍትሕ ሂደት ነው፡፡ ስለሆነም፤ ሂደት እንደመሆኑ ጊዜ የሚፈልግና በጥንቃቄ ሊተገበር የሚገባ የፍትሕ ዓይነት ነው፡፡

የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን ብዙ መንገዶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ፤ አጥፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለተወሰኑአጥፊዎች ምህረት መስጠት፣ ተጎጂዎችን መካስ፣ እውነታው በዝርዝር እንዲገለጥ ማድረግ ወዘተ ሆነውእንደ ሁኔታው አስፈላጊነት አንዱ፣ ኹለቱ፣ ሦስቱ ወይም ከዚያ በላይ ሊተገበሩ ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በአገሪቱ የሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት የጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ በነበሩት ክልሎች ውስጥ ብዙ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች፣ የግለሰብ ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋልም። እንስሳት ሳይቀሩ በቀጥታ በጥይት እየተመቱ ሞተዋል። ይህም ምናልባት በዓለም ላይ በግጭት ጊዜ እንስሳት ሆን ተብሎ ሲገደሉ የመጀመሪያ ሊሆን ይችላል፡፡

በተጨማሪም፤ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ቤተሰብ ፈርሷል፣ግጭቱ በነበረባቸው ክልሎች በሕዝቦች መካከል ያለው ማኅበራዊ ትስስር (social fabric) መበጠሱን/መቋረጡን የሚያሳዩና እንኳን ለማየት ለመስማትም ጸያፍ የሆኑ ብዙየወንጀል ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለምሳሌም ያህል፤ በአገር ውስጥ እና በዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከተረጋገጡትመካከልእንኳ በስብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የጦርወንጀሎችተፈጽመዋል፡፡በተጨማሪም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እስካሁንም በሚሰጣቸው እርዳታና በልመና ለመኖር የተገደዱ ዜጎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት እና እስካሁንም በአሸባሪነት ዝርዝር ወስጥ በሚገኘው በሕወሓት መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት ዘላቂ ሰላም ሊመጣ ነው እየተባለ በሰፊው ሲዘገብ ይሰማል፡፡ ብዙ ሰውም ዘላቂ ሰላም እንደሚመጣ ተስፋ አድርጓል፡፡ ይህ በእንዲህ ሳለ ስለ ዘላቂ ሰላም ሲታሰብ የሚከተሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፤ በጦርነቱ ጊዜ ሕወሓትና አመራሮቹ ላደረሱት ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመት በሕግ ተጠያቂ አይሆኑም? ለተጎጂዎች ካሳ መክፈልስ የለባቸውም? መንግሥትስ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ሊያቋቁም አይገባም? ምንስእቅድ ይዟል? ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ሳይቋቋሙና ወደ ኑሮአቸው ሳይመለሱ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ ይችላል? እና መሰል በርካታ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

በሽግግር ፍትሕ ጊዜ ከሚኖሩና ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ የተጎጂዎች የመካስ መብት ሲሆን በዚህ ጽሑፍ የሽግግር ፍትሕና የመካስ መብትን ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር እንመከለታለን፡፡

የተለያዩ አገሮች ልምድ እና ዓለም ዐቀፍ የሽግግር ፍትሕ መስፈርት ተብለው የተቀመጡእንደሚያሳዩትበተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ከሚያስፈልጉና የግድ ሊሟሉ ከሚገባቸው ሁኔታዎች አንዱ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን የመካስ መብት በማክበር በሚገባው ልክ መካስ ነው፡፡ ለምሳሌም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ. በ2005 ያጸደቀው ሰነድ በቅጭት የተጎዱ ዜጎች በበቂ ሁኔታ የመካስ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡እንዲሁም፤ የአፍሪካ ኀብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከአንቀጽ 64-66 ባለው ስር የግጭት ሰለባ የሆኑ ዜጎች የመካስ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም፤የሰሜኑ ጦርነት ሲጀመር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ጥቃት ተፈጸመበት፡፡ በጊዜውም ፍጹም ከሰብዓዊነትያፈነገጡድርጊቶች በሠራዊቱ ላይ ተፈጽመዋል፡፡ ወታደሮች ሬሳ ላይ ተቀልዷል፣ ተዘፍኗልም። ሴት ወታደሮች ላይ ከጡት መቁረጥ ጀምሮ ለመግለጽ ጸያፍ የሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፤ ቤተሰቦቻቸው ተገድለዋል፣ ልጆች ያለ አሳዳጊ፣ ሚስት ያለ ባል፣ ባል ያለ ሚስት፣ አረጋውያን ያለ ረዳትና ጧሪ ቀርተዋል ወዘተ፡፡ እነዚህ ሁሉና ሌሎችም ግፎች የተፈጸሙባቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ፍትሕ ሳያገኙና ሳይካሱ የሚደረግ እርቅና ሊመጣ ነው የሚባል ሰላም ትርጉምና ውጤት አይኖረውም፡፡

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በማይካድራ፣ በጭና፣ በጋሊኮማና በሌሎችም ቦታዎች ሰዎች በዘራቸው ምክንያት በጅምላ ተገድለዋል፤ የጦር ወንጀል፣ በስብዕና ላይ የተፈጸሙና የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ የተጠቀሱትን በአገሪቱ እና በዓለም ዐቀፍ የወንጀል ሕጎች በከባድ ወንጀልነት የተደነገጉ ድርጊቶችን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ሳይሆኑ፣ ዜጎች ፍትሕ ሳያገኙና ተገቢውን ካሳ አግኝተው ወደ መደበኛ ኑሮአቸው ሳይመለሱ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም፡፡

ዜጎችን የመካስ ግዴታ በዋናነት የመንግሥት ሲሆንመንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወዘተ በሂደቱ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ዜጎች ላይ የደረሰን ጉዳት በሙሉ መካስ አይችል ይሆናል በተለይም ብዙ ጉዳት እና ውድመት ከደረሰ የማይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ባለው አቅም የተቻለውን ሁሉ እንዲሚያደርግና እንዳደረገም ለሕዝብ የሚያሳምን ሥራ መሥራት አለበት፡፡

ከላይ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆነው ስለ ካሳ ሲነሳ በርካታ ሊሟሉ የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩም የሚከተሉት የካሳ ዓይነቶች የግድ ሊሟሉ የሚገባቸውና የተለመዱ ናቸው፡፡

 • ቅድሚያ ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ የደረሰ የጉዳት ዓይነትና መጠን ሊታወቅ ይገባል፡፡የምርመራ ግኝቱም ሊቀርብ የሚገባው ሳይሸራረፍ እንዳለ ሲሆን እውቅና ሊሰጠው የሚገባውም ባለበት ነው፡፡በተጨማሪም በምርመራ ግኝት የመንግሥት ጥፋት ተብለው የተለዩ ችግሮች ካሉም መንግሥት ጥፋቱን በማመን በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዜጎችን መካስ የሚጀመረው ለጉዳታቸው እውቅና በመስጠትና ተገቢውን ይቅርታ በመጠየቅም ነውና፡፡
 • ንብረታቸው የወደመ ዜጎች ንብረታቸው ሊተካላቸውና ሊቋቋሙ ይገባል፡፡
 • ንብረታቸው የተዘረፈ ዜጎች የተዘረፈው ሊመለስላቸው ወይንም ሊተካላቸው ይገባል፡፡እንዲሁም፤ የተቀማ መሬትና ሌላም ሀብታቸው ሊመለስላቸው ይገባል፡፡
 • የተደፈሩ ሴቶች ፍትሕ ማግኘት አለባቸው፣ ነጻ የሕክምና አገልግሎት እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሊደረግላቸውም ያስፈልጋል፡፡
 • የወደሙና የተጎዱ መሠረተ ልማቶች ድጋሚተሠርተውና ተጠግነው ሕዝቡ ወደ ቀደመ መደበኛ አገልግሎት ወደሚያገኝበት ኑሮው እንዲመለስ መደረግ አለበት፡፡
 • የሕዝብ የሆኑ የአገልግሎት ተቋማት እንደ ሕክምና፣ ውሃ፣ መብራት፣ ፋብሪካዎች የመሳሰሉት ወደ ሥራ ሊመለሱና ሕዝብ አገልግሎት ማግኘት መጀመር አለበት፡፡
 • በሕወሓት ወታደሮች የሃይማኖት ተቋማት ተዘርፈዋል፣ ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ተደርገው ነበር፣ መስጊዶችና አብያተ ክርስቲያናት በከባድ መሣሪያ እየተመቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ካህናት ተገድለዋል፣ መነኮሳት ተደፍረዋል፣ ሌሎችም ጸያፍ ወንጀሎች በእምነት ተቋማት ላይ ተፈጽመዋል፡፡ ስለሆነም፣ እርቅና ዘላቂ ሰላም ሲባል የሃይማኖት ተቋማት ለተፈጸሙባቸው ወንጀሎች ፍትሕ ሊሰጣቸው፣ ተቋማቱና ምእመኖቻቸው በይፋ ይቅርታ ሊጠየቁና ተገቢውም ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡
 • ክልሎች ተዘርፈዋል፡፡የሕወሓት ወታደሮች ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድየጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሌሎችም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ እና የልማት ድርጅቶችን ዘርፈዋል፡፡ የዘረፏቸውን ንብረቶችም እንደ ራሳቸው አድርገው አሁን በትግራይ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት፣ የመንግሥት ቢሮዎች እና ሌሎችም ተቋማት ውስጥ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ የአማራ እና አፋር ክልሎች የጤና ተቋሞቻቸው ተዘርፈውና ወድመው ዜጎች በሕክምና መሣሪያና መድኃኒት እጦት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆሳለ፤ የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት ደግሞ ከኹለቱ ክልሎች በዘረፏቸው ማሽኖችና ሌሎች ቁሳቁሶች ሕዝባቸውን እያከሙ፣ የአማራ እና አፋር ክልሎች ትምህርት ቤቶቻቸውና የመንግሥት ተቋሞቻቸው ያለ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ያለ ኮምፕዩተርና ሌሎችም ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ባለመኖራቸው ሕዝብ እየተንገላታ ባለበት፤ ነገር ግን የትግራይ ክልል ባለሥልጣኖች ከኹለቱ ክልሎች በተዘረፉ ንብረቶች የትምህርትና ሌሎች ተቋማትን ለማስጀመር እየተንቀሳቀሱ ባለበት ሁኔታ በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረገው እርቅ ምን አዎንታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢነው፡፡

ስለሆነም፤ ስለ ዘላቂ ሰላም እና እርቅ ሲወራ ከክልሎች የተዘረፉ ንብረቶችን ከሕወሓት ስለማስመለስም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን በክልሎችና በሕዝቦች መካከል ቅራኔው ስለሚዘልቅ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሰላም ስምምነት ቢደረግ ከፖለቲካ ወሬነት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም ሁኔታው ለወደፊቱ መሰል ወንጀል ለሚፈጽሙ እንደ ኦነግ ያሉ ቡድኖች መጥፎ ምሳሌ ይሆናል፡፡

 • ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሊመለሱና የቀደመ ሕይወታቸው እንዲቀጥል መቋቋም አለባቸው፡፡ተመልሰው መቋቋም ብቻ ሳይሆን በፊት የተፈጸመባቸው ወንጀልና እንግልት ድጋሜ እንደማይፈጸምባቸው መንግሥት ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሽግግር ፍትሕ ማለት “ያለፈው አይደገምም” ተብሎ ቃል የሚገባበትም ነውና፡፡
 • በቀውሱ ምክንያት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ነጻ ወይም አቅማቸውን የሚመጥን የሕክምና አገልግሎት ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡
 • በግጭት ምክንያት በአስገድዶ መደፈር፣ ቤተሰባቸውን በማጣትና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ነጻ የሥነ-ልቦና ሕክምና እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
 • በግጭቱ ምክንያት ትምህርታቸው የተቋረጠ ዜጎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ እንዲሁም ነጻ የትምህርት እድል ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡
 • በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውንና የዓመት ልብሳቸውን ወጪ የሚሸፍኑበት እንዲሁምራሳቸውን ችለው መኖር እንዲጀምሩ ለማስቻል የሥራ እድልም ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡
 • ከፍተኛ እና ዘላቂ የሆነ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በአካል ማገገሚያ ተቋም ገብተውእርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
 • በጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ክልሎች እንዲያገግሙ ለማገዝ መንግሥት ከሚመድብላቸው መደበኛዓመታዊ በጀት በተጨማሪ ድጎማም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
 • በማቋቋሙ ሂደት መንግሥት ክልሎችን እና ሕዝቦችን እኩል መደገፍ አለበት፡፡ ስለሆነም፤ አንዱን ክልል እና ሕዝብ ከሌላው በተለየ መደገፍ፣ ሌላውን ደግሞ ችላ ማለት ዘላቂ ሰላም ከማምጣት ይልቅ ዘላቂ ቁርሾ የሚፈጥር ይሆናል፤ ጊዜውን ጠብቆም አገሪቱን ወደ ሌላ ዙር የከፋ ግጭት የሚከት ስለሚሆን በመንግሥት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

በግጭት ጊዜ የተጎዱ ዜጎችን ስለ መካስና መልሶ ማቋቋም ሲነሳ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችና ልምዶች እንዲሚያሳዩት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ጉዳት ያደረሱ አካላት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመካስና በማቋቋም ሂደት እንዲሳተፉ ሊደረግ ይችላል/ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር ሲገለጽም፤ ሕወሓት ጉዳት ላደረሰባቸው ክልሎችና ዜጎች ካሳ እንዲከፍል እና መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥም እንዲሳተፍ የሚደረግበት አግባብ ስላለ መንግሥት ስለ እርቅና ዘላቂ ሰላም ሲያስብ ይህን ሁኔታም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡

ከላይ የተገለጹት እንዳሉ ሆነው የሕወሓት ኃይሎች ፈጸሙ ለተባለው ወንጀልና ግፍ ሁሉ ዋና አዛዥ የሆኑትን ባለሥልጣኖች ለፍትሕ ማቅረብ ሕዝብን እና የተጎዱ ዜጎችን የመካስ አንዱና ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሽግግር ፍትሕ በባህሪውለተጎጂዎች ቁሳዊ ካሳ በመስጠት ብቻ ሊሳካ የሚችል አይደለም፤ ፍትሕ በመስጠትም ጭምር እንጂ።

ስለሆነም፤ ስለ ሽግግር ፍትሕ ሲነሳ በኢትዮጵያና በዓለም ዐቀፍ የወንጀልሕጎች የተደነገጉ ወንጀሎችን በመፈጸም የተጠረጠሩ የሕወሓት ባለ ስልጣናትን ለፍትሕ ማቅረብን መንግሥት የግድ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ባለሥልጣናቱን በምህረት ከተጠያቂነት ነጻ ማድረግና ለዘላቂ ሰላም በሚል ሽፋን ሹመት ወደ መስጠት የሚገባ ከሆነ የአገሪቱን የሳሳ የሰላም አየር ከድጡ ወደ ማጡ ሊከት የሚችልና ወደ ፊት ለሚፈጠር ከፍተኛ ግጭት መንስኤ ስለሚሆን በመንግሥት ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ማለፍ ካለባት የሕወሓትና የብልጽግና መታረቅ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የኹለቱ ቡድኖች መታረቅና በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች የጥይት ድምጽ አለመኖሩ ብቻ ለአገር ዘላቂ ሰላም አያመጣም፡፡ ይልቁንም በሌሎች ክልሎች ውስጥ ያሉ ዜጎችም ደኅንነት መጠበቅ አለበት፡፡ በቤኑሻንጉል ክልል የዜጎችን ደም ያፈሰሱ አካላት ለፍትሕ ሊቀርቡና በእነሱ ምክንያት የተጎዱ ዜጎችም ሊካሱና ወደ መደበኛ ኑሮዋቸው ሊመለሱ ይገባል፡፡ በተጨማሪም፤ በኦሮሚያ ክልል በኦነግ ሸኔና በሌሎችም የተደራጁ ግለሰቦችና ቡድኖችየሚፈጸም የዜጎች መፈናቀልና ሞት መቆም አለበት፡፡ የወለጋን ወንጀል የኢትዮጵያ ሕዝብም ዓለምም ስላየውና ስለሰማው መንግሥት ቢያምንም፣ ነገር ግን በክልሉ ሌሎች ቦታዎችም መፈናቀልና ሞት ቀጥሏል፡፡

ለምሳሌ ያህል፤በሰሜን ሸዋ በየዓመቱ የተቀናጀ ጥቃት በሕዝብ ላይ ይፈጸማል፣ ከተሞችም ይወድማሉ፤ በምሥራቅ ሸዋም በተለያዩ ቦታዎችሰዎችን እያገቱ ገንዘብ መቀበል፣ ገንዘብ ከተቀበሉም በኋላመግደል፣ ማፈናቀል፣ የዘር ማጽዳትና ሌሎችም አደገኛ ወንጀሎች እስከ አሁን እየተፈጸሙ ስለሆነ መንግሥት በአፋጣኝ ሊያስቆምና ዜጎችን ወደ ኑሮዋቸው ሊመልስ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በመንግሥት አካላትና በተለያዩ ቡድኖች በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚደረግ ጣልቃገብነት ሙሉ በሙሉ ሊቆም ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት ግጭት ከዘር ግጭትም በላይ ኢትዮጵያን ችግር ውስጥ መክተት ይችላል፡፡ለተጠቀሱት ሁሉ ችግሮች ሳይረፍድ መፍትሔ ካልተፈለገ ቀውስ ሽብርን እንጂ ሰላምን አይወልድም፡፡

ከላይ የተጠቀሱ በርካታድጋፍ የሚገባቸው ዜጎች እገዛ ሳይደረግላቸው፤ ድጋፍ አግኝተው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ሳይደረግ ሰላም አውርደናል ብሎ አለባብሶ ማለፍ ሌላ ምሬትና የበቀል ስሜትን ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ለዘላቂ ሰላም ምንም ጥቅም የለውም፡፡ሁኔታውም የሽግግር ፍትሕ ሳይሆን “የሽግግር በደል” ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞት ምክንያት የሆነውን ጦርነት ያስነሱትን፣ ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደሆነና ዓላማቸውን ለማሳካትም ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ጋርም መሥራት ካለባቸው ሲዖል ለመውረድ እንደማያመነቱ ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተው እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ዝተውየተንቀሳቀሱ፤ ምንም እንኳ አገር ማፍረሱ ባይሳካላቸውም ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ብዙ ወንጀሎችና በደሎችን በአገር እና በሕዝብ ላይ የፈጸሙ የሕወሓት ባለሥልጣኖችን”ለዘላቂ ሰላም ሲባል” የሚሉና ሌሎች ድሪቶ ምክንያቶችን በመስጠት በሕግ እንዳይጠየቁ በማድረግበመከላከያ ሠራዊትና በሌሎች ዜጎች ደም ላይ ለመፍረድ የሚያስችል የሕግ መሠረት የላቸውም።

ሥልጣን በእጃችን ስላለ ምንም አይመጣብንም በሚል አስተሳሰብ ከተወሰነምዳፋው ለትውልዶች የሚተርፍ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በሽግግር ፍትሕ መርህ መሠረት ተገቢው ሕክምና ያልተደረገለትና ሳይድን በግድ እንዲሸፈን ተደርጎ የታለፈ የሕዝብ ቁስል ማመርቀዙ አይቀርም፡፡

ስለሆነም፤ ምንም እንኳ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የሕግ ማእቀፍ በሽግግር ፍትሕ ጊዜ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ካሳ ስለሚያገኙበት ሁኔታ የሚዘረዝር ሕግ ባይኖርም፤ ዓለም አቀፍ ሕግናልምዶችን በማየት መንግሥት ተጎጂዎችን የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠንና ሌሎች አካላትንም በማስተባበር ሊክስ፣ ወደ ቀደመ ኑሮአቸው ሊመልሳቸውም ይገባል፡፡

በመጨረሻም፤ በተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ለማለፍከላይ በሕወሓት አመራሮችና ሠራዊት እንዲሁም በኦነግ ሸኔ ተፈጸሙ ለተባሉ ወንጀሎች ፍትሕና ካሳ ይገባል የተባለው በትግራይ ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በሌሎችም የታጠቁ ግለሰቦችና ቡድኖች ለተፈጸሙ ወንጀሎችና ለደረሱ ጉዳቶችም በተመሳሳይ መልኩ ሊተገበር ይገባል፡፡

ሽመላሽ ወንዳለ፡ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ኹለተኛ ዲግሪበኢሜል አድራሻቸው shiwondale@gmail.com ይገኛሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here