በአዲስ አበባ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተገለጸ

0
1738

ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲሱ ስርዓተ ት/ት መሰረት በአማርኛ ቋንቋ ለሚማሩ ተማሪዎች አፋን ኦሮሞ፣ በአፋን ኦሮሞ ለሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ አማርኛ ት/ት መስጠት መጀመሩን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡

በከተማዋ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ ከመሰቀል፣ እንዲሁም ከክልሉ መዝሙር ጋር በተገናኘ ውዝግብ መፈጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ ችግሩ ያጋጠመው ከተማ አስተዳደሩ በት/ት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ተከትሎ፣ የቋንቋውን ትምህርት ካሪኩለም ከእነ ክልሉ መዝሙር ተውሶ አዲስ አበባ ላይ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ ነበር፡፡

የከተማ አስተዳሩ ይህንኑ ችግር ያስቀራል ያለውን በአዲስ አበባ ት/ት ቤቶች ከአፍ መፍቻ ቋንቋ በተጨማሪ፣ ሌላ ቋንቋ እንዲሰጥ የሚፈቅድ በጥናት ላይ የተመሰረተ ነው ያለውን አዲስ ስርዓተ ት/ት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሄው ስርዓተ ት/ት መደበኛ ትምህርታቸውን በአማርኛ ቋንቋ ለሚማሩ ተማሪዎች አፋን ኦሮሞ፣ እንዲሁም በአፋን ኦሮሞ የሚማሩ ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን እንደ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲማሩ የሚያደርግ ነው፡፡

ስርዓተ ትምህርቱ በቅርቡ በተጀመረው ኹለተኛ ሴሚስተር ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ት/ት ቤቶች መምህራን ሰምታለች፡፡ የተጨማሪ ቋንቋ ትምህርት ስርዓቱ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በሦስተኛ እና አራተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው ተብሏል።

በኹለቱም በኩል ተጨማሪ ቋንቋውን የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርቱ በተጀመረባቸው ደረጃዎች ማለትም 3ኛ እና 4ኛ ክፍል የሚማሩ ሁሉም ተማሪዎች ናቸው፡፡ የቋንቋ ትምህርቱ በሂደት የሚሰፋ መሆኑ የገለጸ ሲሆን፣ አፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚችሉ መምህራን በስፋት መቀጠራቸውንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡ በአንዳንድ ት/ት ቤቶች ቀድሞውንም የነበሩ አፋን ኦሮሞ የሚችሉ መምህራን በአማርኛ ከሚሰጡት ት/ት በተጨማሪ የተጀመረውን የአፋን ኦሮሞ የቋንቋ ት/ት እያስተማሩ እንደሚገኙም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግበራዊነት፣ በከተማዋ ላይ ስጋት ፈጥሮ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማና መዝሙር ውዝግብ ማስቀረቱን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው መምህራን ሰምታለች፡፡ መምህራኑ እንደሚሉት፤ በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ከኹለተኛ ሴሚስተር በኋላ ቀድሞ በኢትዮጵያ ሰንደቅ  ጋር አብሮ የሚሰቀለው የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅና የሚዘመረው የክልሉ መዝሙር መቋረጡን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረው ግጭት እንዳያገረሽ በመስጋት፣ በአንዳንድ ት/ት ቤቶች ተማሪዎች መዝሙር ሲዘምሩ ባንዲራ የማይሰቀልበት ሁኔታ መኖሩ ታውቋል፡፡ በዚህም የተለመደው ኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ቀርቶ የኢትዮጵያ ብቻ ሲሰቀል ችግሩ እንዳያገረሽ በሚል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ተማሪዎች ለመዝሙር ሳይሰበሰቡ አስቀድሞ እንደሚሰቀልም አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here