ዳሰሳ ዘ ማለዳ ጥቅምት 28/2012

0
954

1-የትዊተር መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃክ ዶርሴይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የአፍሪካ አገራትን በዚህ የህዳር ወር እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።ጉብኝታቸውንም በናይጄሪያ የጀመሩ ሲሆን በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ በማምራት ከሥራ ፈጣሪዎች ጋር እንደሚወያዩም በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።ከኢትዮጵያውያኑ የቴክኖሎጂ የሥራ ፈጣሪ ወጣቶች፣ ቤተልሄም ደሴ፣ ኖኤል ዳንኤል እና ጌትነት አሰፋ ጋር ሰፊ ቆይታ እንደሚኖራቸው ነው ጃክ ዶርሴይ የገለጹት።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………..
2-በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የራስ አበበ አረጋይ መኖርያ የነበረው ቤት ይዘቱን ሳይቀይር የጤና እና ጤና ጋር ተዛማጅ የሆኑ መረጃዎች ማከማቻ /data center‬/ እንዲሆን ተደረገ። በውስጡም የስልጠና ማዕከል ፣ የሶፍትዌር ልማት /software development/ ፣ ጤና ላይ የሚሰሩ የኤሌክትሮኒክ ሲስተም ላይ መረጃ የሚሰጥ የ24 ሰዓት የጥሪ ማዕከል እና የምርምርና የልዕቀት ማዕከል እንደሚኖረው የጤና ሚንስትር ዶ/ር አሚር አማን ገልጸዋል።የእድሳትወጪውም በጤና ሚኒስቴር እና በአጋር ድርጅቶ ትብብር ተሰርቶ መጠናቀቁንም ተናግረዋል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
3-በአምባሳደር ብርቱካን የተመራ ልኡክ በእስራኤል ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል የጉብኝቱ ዓላማ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ መንግስት ንብረት የሆኑትንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚተዳደሩትን ህንፃዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በመገምገም፣ ታሪካዊ ይዘታቸው እንደተጠበቀ የሚታደሱበትንና ለአገር ብሄራዊ ጥቅምና ክብር የሚያስገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

http://addismaleda.com/archives/7920
……………………………………………………………..
4-ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በተያዘዉ የሩብ በጀት ዓመት 168 ሚሊዮን 953 ሺሕ ብር የቦንድ ግዥ መፈፀሙን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።ጽሕፈት ቤቱ ዛሬ ጥቅምት 28/2012 በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በሰጠው መግለጫ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከሕዝቡ 13 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጿል።የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ሀይሉ አብራሃም እስካሁን ድረስ ወደ 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚሆን ቦንድ ለግለሰቦች መመለሱንም ተናግረዋል።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………..
5-የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ደረጃ ኹለተኛ የሆነውን የምስለ ሕክምና ማዕከል ጥቅምት 27/2012 አስመርቆ ወደ ሥራ ማስገባቱን አስታውቋል።ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ምስለ ሕክምና ማዕከል በንድፈ ሐሳብ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የሰመመን ሰጭ (አንስቴዢያ) ሕክምና ትምህርት ለመምህራንና ተማሪዎቻቸው በተግባር የተደገፈ እንዲሆን የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።ማዕከሉ ‹‹ኢምፓክት አፍሪካ›› በተባለ ድርጅት አማካኝነት ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በኢትዮጵያ የተቋቋመ መሆኑን አስታዉቀዋል።(አብመድ)
……………………………………………………………..
6-የተሰረቁ ቼኮችን እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ 60 ሚሊዮን 843 ሺሕ 601 ብር ያጭበረበሩ ከ70 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።በወንጀል ፈፃሚዎቹ ሊወሰድ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም በኮሚሽኑ የከባድ ሌብነትና ዘረፋ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ ገልፀዋል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
7-በአማራ ክልል በቀወት ወረዳ የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የወፍ መንጋው አስካሁን በሰብል ላይ ያስከተለው ጉዳት በውል ባይታወቅም ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የቀወት ወረዳ ግብርና ምፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ማምሻ አስረድተዋል። 6ሽሕ የሚጠጋ የግሪሳ ወፍ መንጋ ተከስቷል።(አብመድ)
……………………………………………………………..
8-ሕብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ሕንጻ ለሥራ ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ።ከተመሰረተ 25 ዓመታትን ያስቆጠረው ኩባንያው በ2 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እና 17 ወለል ያለዉን የህንፃ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቁን አስታውቋል።(ዋልታ)
……………………………………………………………..
9-በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረስብ አስተዳደር በአካባቢው ከተከሰተው ድርቅ ጋር ታያይዞ ትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በቅርብ ካልተጀመረ ትምህርት ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተማሪዎችና መምህራን ተናገሩ።የዞኑ ትምህርት መምርያ በበኩሉ ችግሩ በስፋት ተከስቶባቸዋል በተባለዉ 81 ቀበሌዎች ጥናት መደረጉንና እቅድ የተዘጋጀ ሲሆን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ታኅሳስ ወር ላይ የምገባ ፕሮግራም አንደሚጀምር አስታውቋል።(ዶቼ ቬሌ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here