የሰብኣዊ መብት ጥሰት አለመቆሙን ከእስር የተፈቱ ዜጎች ተናገሩ

0
746

ባለፉት አራት ወራት በሰኔ 15ቱ የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረጉ ተጠርጣሪዎች የእስር ቤት ቆይታ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሁኔታ፣ የምርመራ ሂደትና የፍርድ ቤት ሥነ ስርዓት ላይ ግድፈቶች እንደነበሩ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ አሁንም መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አስታወቁ።

ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ዲፕሎማቶችና እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወኪሎች በተገኙበት በቅርቡ ከእስር የተፈቱት እና በባልደራስ ምክር ቤት የተሰበሰቡ ግለሰቦች አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት አባላትም ለወራት ታስረው የቆዩ ሲሆን፣ በጨለማ እስር ቤቶች መቆየትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ማረፊያ ቤት ጨለማ ቤት ከ አንድ ወር ጊዜ በላይ እንደተቀመጡ እና ለሦስት ወራት ግን ወደሌላ ስፍራ እንዲወሰዱ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ 22 ሰዎች አቃቤ ሕግ ክስ ያልመሰረተባቸው እንደሚገኙ በመድረኩ ላይ ተገለጿል።
‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ ማዕከላዊ ከተዘጋ በኋላ ከፍተኛ የሰዎች ስቃይ የሚፈጸምበት ስፍራ እየሆነ መምጣቱን ለዚህም ማሳያው የጨለማ ቤቶች መኖራቸው፣ ተጠርጣሪዎችን ለሊት እየተጠሩ ምርመራ መደረጉና በምርመራ ሂደቱ የፖለቲካ አባልነት ጥያቄ የሚነሳበት የፋይናንስ ምንጭ የሚጠየቅበት የፖለቲካ ጫና ያለበት ምርመራ ስለሆነ ነው›› ሲሉ የባላደራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል ይገልጻሉ።

በመሆኑም መገናኛ ብዙኀኑ እንዲያውቁ የተደረገው እስረኞች የሥነ ልቦና ጫና የተደረገባቸው መሆኑን ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይነትም በእስር ያሉ ዜጎች እንዲፈቱ ድምጽ ለማሰማት እና ጫና ለመፍጠር መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here