ሐሙስ ሚያዚያ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለኹለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሦስቱ ክልሎች አንዱ ለሆነው ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ አገር አቀፍ የሀብት ማሰባሰብ መድረኮች ሊዘጋጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመነጋገር በተለያዩ ጊዜያት በአገር አቀፍ ደረጃ ይህን የሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ እንደሚያካሂድ ትግራይ ቴሌቪዥን በዘገባው አመላክቷል፡፡
ሆኖም የሀብት ማሰባሰብ መድረኩ መቼ እና እንዴት እንደሚዘጋጅ በግልጽ አልተጠቀሰም፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ በፌደራል መንግሥቱ ሲገነቡ የነበሩ እና በጦርነቱ ምክንያት ግንባታቸው የቆሙ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደገና ለማስጀመር በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በማዕከላዊ መንግሥቱ ዘንድ ከስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም በርከት ያሉ የውሃ፣ የጤና እና የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ዳግም እንደሚጀመር የተጠቀሰ ሲሆን፤ ለአብነትም የመቀሌ የገረብ ግባ፣ የአክሱምና የአዲግራት የውሃ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የአድዋ ሆስፒታልና የአክሱም ላብራቶሪ ማዕከል እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱን እና የህወሓትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለክልሉ ከተፈቀደው የ2015 በጀት የተወሰነው ተለቆ ሥራ ላይ መዋሉንና ቀሪው ደግሞ በቅርቡ እንደሚለቀቅም ተጠቁሟል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግሥቱ እያደረጉ ባሉትና ወደፊትም በሚያደርጓቸው ተከታታይ የፖለቲካ ውይይቶች የ2014 በጀት ጥያቄን ጨምሮ መፍትሄ የሚያገኙ በርከት ያሉ ጉዳዮችም ይኖራሉ ነው የተባለው፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የ2014 በጀት ዓመት ገንዘብ እንዲለቀቅለት ለማዕከላዊ መንግሥቱ ጥያቄ ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፤ በ2014 እና 2015 በጀት ዓመት ክልሉ ማግኘት ለነበረበት የትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በጀትም ከመጭው ዓመት በጀት ላይ እንዲሚጠይቅ ተመላክቷል፡፡



