የኦሮሞ ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት እና የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ አብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ

0
563

ሰኞ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ የባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ማዕከል እና የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ በዘርፉ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

በኦሮሞ የባህል ማዕከል እየተካሄደ ባለው ውይይት በአፋን ኦሮሞ የተጻፉ ታሪኮች እና ቅርሶች በስጦታ መልኩ ለትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ተበርክተዋል።

የኦሮሞ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዝናቡ አስራት፤ የኹለቱን ክልሎች ቋንቋዎች፣ ባህል እና ታሪክን ለማሳደግ በጥናት እና ምርምር የታገዘ ሥራ እንሠራለን ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዲሪባ ተፈራ በውይይቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችም አፋን ኦሮሞን፣ የኦሮሞን ባህል እና ታሪክ አስመልክቶ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል ተክሉ አካዳሚው በ2008 የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፤ የትግራይ ቋንቋዎችን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ የተለያዩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‹‹ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያለንን ወንድማማችነት እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከርም ከኦሮሞ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እንሠራለን፡፡›› ሲሉም መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ባለፉት 2 ዓመታት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሥራዎች ሳያከናውን መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የኦሮሞ ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ለማዕከሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here