የራይድ ሾፌሩን በሽጉጥ አስፈራርቶ መኪናውን ይዞ የተሰውረው ግለሰብ በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ ተቀጣ

0
509

ማክሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ የራይድ አገልግሎት እየሰጠ ባለው ተሽከርካሪ በመግባት በሽጉጥ አስፈራርቶ ሾፌሩን አስወርዶ ተሽከርካሪውን በመውሰድ የራሱ ያልሆነውን የሰሌዳ ቁጥር ለጥፎ በተገኘውና በተሽከርካሪው ውስጥ የነበረውን ኤቲኤም ካርድ በመጠቀም ከተበዳይ የሒሳብ ቁጥር 50 ሺሕ ብር በወሰደው ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶ በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ10 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ግለሰቡ ከህዝባዊ መብቱ ለ3 ዓመት ታግዶ እንዲቆይ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኖበታል፡፡

ማርቆስ ጡምደዶ ጊባንቾ የተባለው ተከሳሽ መጋቢት 26/2014 በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ጀሞ ቆሼ ታፍ ነዳጅ ማደያ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፤ የግል ተበዳይ ያሬድ መንግስቱ ኮድ 3 አዲስ አበባ የሆነ ቪትዝ መኪና ይዞ የራይድ አገልግሎት ለመስጠት እያሽከረከረ እያለ፣ ተከሳሹ ጀሞ አካባቢ መንገድ ላይ ቆሞ በመጠበቅ የግል ተበዳይን በማስቆም አየር ጤና እንዲወስደው ጠይቆ በተሽከርካሪው ከኋላ በኩል መግባቱን ዐቃቤ ህግ ገልጿል።

በማስከተልም አየር ጤና አካባቢ ሲደርሱ <<ደርሻለሁ አቁምልኝ>> በማለት ከኋላ በኩል ሽጉጥ በመደገን <<እገድልህ ነበር አሳዝነኸኝ ነው አሁን ከመኪናው ውረድ>> በማለት እንዲወርድ ካደረገ በኋላ፤ በውስጡ የግል ተበዳይ መንጃ ፈቃድ፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የአዋሽ ባንክ ኤቲኤም ካርድ ከነሚስጥር ቁጥሩ የያዘውን ተሽከርካሪ ይዞ ይሰወራል።

በዚህም የመኪናውን የሰሌዳ ቁጥር ቀይሮ ለጥፎበት እያሽከረከረ ታይቶ እያሽከረከረ ሊያመልጥ ሲል በአካባቢው ሰዎች በተደረገ ርብርብ መኪናውን ጥሎ ያመለጠ ሲሆን፤ ነገር ግን በመጨረሻ በቁጥጥር ሥር ውሎ የወንጀል ህጉን አንቀጽ 671(1) ለ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈጸመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

በዚህም በመኪናው ውስጥ ያገኘውን የተበዳይ ኤቲኤም ካርድ በመጠቀም ከተበዳይ ሒሳብ ቁጥር ላይ ሀምሳ ሺሕ ብር የወሰደ በመሆኑ የብሔራዊ የክፍያ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 አንቀጽ 35/4/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው የተሰረቀ የክፍያ ሰነድ መጠቀም ወንጀል እንዲሁም፤ የተሽከርካሪውን ሰሌዳ ቁጥር ቀይሮ በመለጠፍ ተሽከርካሪውን የተጠቀመበት በመሆኑ የተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመሪያና መመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 681/2002 አንቀጽ 48/2/ለ/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈጸመው አንድን ተሽከርካሪ የራሱ ያልሆነውን የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ለጥፎ መገኘት ወንጀል 3 የተለያዩ ክሶች  ቀርበውበታል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በዐቃቤ ህግ የቀረቡትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል በሰጠው ብይን መሰረት ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ላይ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የመከላከል መብቱ ታልፎ በ3ቱም ካሶች ጥፋተኛ በማለት ሚያዚያ 17/2015 ባስቻለው ችሎት  ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንዲሁም ከህዝባዊ መብቱ ለ3 ዓመት ታግዶ እንዲቆይ ሲል መወሰኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here