ነገረ ታሪክ ዘኢትዮጵያ ከዛሬ የሚያዘናጋ ከነገ የሚያዘገይ

0
1825

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቀሴ ውስጥ ታሪክ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋስኦ ሆኖ ወጥቷል። ከአኩሪ እና በጎ ታሪካችን በላይ መጥፎው ታሪካችን ትኩረት ተሰጥቶት ከመነጋገሪያነት እና መጨቃጨቂያነት በላይ የግጭት መንስዔ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ታሪክ በራሱ ምንድን ነው ከሚለው በመጀመር የታሪክ አዘጋገብና ፋይዳውን፣ ታሪክንና ኢትዮጵያን፣ የታሪክ አጨቃጫቂነትና የፖለቲካ አጀንዳ አስፈጻሚትን እንዲሁም ለታሪክ አጻጻፍ መፍትሔ ናቸው የተባሉ ምክረ ሐሳቦችን አካታ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ የታሪክ መጽሐፍትን አንብባ እና የታሪክ ባለሙያዎችን አነጋግራ ርዕሱን የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጋዋለች።

“በዚህ ዓለም የሚኖር ሰው ማንም ትልቅ ጌታ ቢሆንና ምንም ገንዘቡ ቢበዛ በግምጃ ቤቱ ያለውን ገንዘቡንና ዕቃውን ቢቻለው በዝርዝር፣ ባይቻለው በድምር ማወቅ ይገባዋል። በግምጃ ቤቱ ያለውን ገንዘቡንና እቃውን ድምሩን እንኳ የማያውቅ ሰው ግን እንደ እንስሳ ይቆጠራል። ትርጓሜውም ያቀረቡለትን ብቻ የሚበላ ማለት ነው። እንደዚሁ ሁሉ ግምጃ ቤታችን አገራችን ኢትዮጵያ ስለሆነች ገንዘባችንና እቃዎቻችንም ነገሥታቶቿ ናቸውና በኢትዮጵያ የነገሡትን ነገሥታት ሥማቸውንና ሥራቸውን ቢቻለን በዝርዝር ባይቻለን በድምር ማወቅ አለብን።”

ይህ ሐሳብ ሰፍሮ የሚገኘው “ዋዜማ” በተሰኘው ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ባስነበቡትና በ1921 በታተመ መጽሐፍ ውስጥ ነው። መጽሐፉ ከነገሥታት ጋር የሚገናኝ ከመሆኑ ሌላ በዚህ ሐሳብ ኅሩይ በድምሩ የቀደመን ታሪክ የማወቅን ጥቅም ቁልጭ አድርገው ገልጸዋል። ታድያ ታሪክን ማወቅ ጠቃሚ ነገር መሆኑ የማያከራክር ሆኖ ሳለ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እና የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በ”ታሪክ” መነሻነት ከዛሬ ታጉለው ከነገም ተስተጓጉለው ይታያሉ። ይህ የታሪክ ዓላማ ነውን?

ታሪክ ምንድን ነው?
መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” (2008) በሚለው መጽሐፋቸው ታሪክን እንዲህ ሲሉ ተርጉመውታል። “ታሪክ የሕዝብ፣ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ፣ ኑሮ፣ ትግል፣ ተጋድሎ ነው። እያንዳንዱ የቀደመው ትውልድ ኅብረቱን፣ ንብረቱንና መብቱን በአጠቃላይ የአብሮ መኖር ህልውናውን አረጋግጦ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላለፈውንና ያስተላለፈበትን ሁኔታ ጭምር የሚገልጽ ቅርስ ነው። ተከታዩ ትውልድ ከቀደመው ትውልድ የተረከበውንና ራሱ ደግሞ የጨመረውን እያካተተ የሚተርክ ዘገባ ነው”

በዚሁ የታሪክ ምንነትና ትርጓሜ ላይ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት ታሪክ አጥኚውና የሚድያ ባለሙያ ሳሙኤል አሰፋ በበኩላቸው፤ ታሪክ በአውሮፓውያኑ የቃል አጠቃቀም “ሂስትሪ” የሚባል ሲሆን በምርምር የሚገኝ እውቀት የሚል ትርጉም አለው ብለዋል። አክለውም “ታሪክ ያለፈው ዘመን ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት በአፈታሪክ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በዐይን ምስክሮች፣ በአርኪዮሎጂካል ቁሶች እና ቅሪቶች ሊረጋገጥ የሚችል ነው” ሲሉም ይገልጻሉ።

በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ታምራት ገብረማርያም ደግሞ፤ ታሪክ የሚባለው እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ በትውልድ መካከል ቆሞ ያለፈውን ለአሁኑ የሚያስረዳና ያለፈውን የሚያጠና ነው፤ ለዚህም የሚጠቀማቸው ቅሪቶች አሉ፤ እነዚህን በመተንተን አንጻራዊ እውነታን የመፈለግ ሁኔታ ነው ታሪክ ወይም የታሪክ ጥናት የሚባለው ብለዋል። በታሪክ መሠረታዊ ጉዳይም ካለፈው ትውልድ የቀጠሉና የተለወጡ ነገሮችን ማየቱ ነው፤ ትላንትና እና ዛሬን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፤ ታሪክ።

ለታሪክ የተለያዩ የሚመስሉ ግን ተመሳሳይ ትርጓሜዎች ተሰጥተዋል። በዚሁም ቀደም ሲል በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀንና ጋዜጦች ከወጡ ዘገባዎችም እናጣቅስ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲናገሩ፤ “ለእኔ ታሪክ ማለት ያለፈ ትዝታ ነው። መጥፎም ጥሩም ትዝታዎች አሉን። እነዚህ ትዝታዎች እንዳይኖሩን ማድረግ አንችልም” ይላሉ። በዚህም ታሪክን እውቀት እንጂ እምነት ማድረግ እንደማይገባ ያሳስባሉ።

በዚህ መሠረት መዛግብትም ሆኑ የታሪክ ሰዎች ታሪክ ያለፈውን ማወቅ መሆኑንና ይህም ለተሻለ ጥቅም እንደሆነ ይነግሩናል። ነገር ግን ያለፈ ነገር ሁሉ ደግሞ ታሪክ እንዳልሆነም የሚያሳስቡ አሉ፤ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ሰለሞን ተሰማ ጂ. “ታሪክ ያለፈውን የሰው ሥራ የሚገልጽ ነው። ሆኖም፣ ያለፈ ነገር ሁሉ ታሪክ አይደለም። ያለፉ ነገሮች በታሪክ ዓምድ ተቀርጸው ለመኖር ሦስት መስፈርቶች የግድ ያስፈልጋሉ” ሲሉ “የታሪክ ዘይቤ” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ ጠቅሰዋል።

አንደኛው ድርጊቱ በተወሰነ ቦታና ጊዜ ለመፈጸሙ እርግጠኛ መሆን መቻል ነው። ይህ ነገር ነው ታሪክን ከአፈታሪክ የሚለየው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት መምህር ታምራት ሲናገሩ፤ ታሪክ አተራረኩ ጥበባዊ ቢሆንም ከተረክ በተለየ ግን መረጃ ላይ መሠረት ያደረገ ነው ይላሉ። ቢሆንም ግን በአፍ ቅብብል የሚኖር ተረክም ቢሆን የማኅበረሰቡን ትዝታና ትውስታ ሊይዝ እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

በሰለሞን ተሰማ ገለጻ መሠረት ደግሞ ሌላው አንድን ኹነት ታሪክ የሚያሰኘው ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ መሆኑ ሲሆን ሦስተኛው ምን ያህል አስፈላጊ ነው ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ሰጪ ሆኖ ሲገኝ ነው። አለበለዚያ ግን አንድ ድርጊት ታሪክ ሊባል አይቻልም።

በዚሁ ላይ የመስፍን ወልደማሪያምን ሐሳብ እንጥቀስ። ቀደም ብሎ በተጠቀሰው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ታሪክ የኹነቶች ድርደራ አይደለም ይላሉ። የተዋናዮቹን አስተሳሰብና ስሜት ጨዋነትና ብልግና የሚሉትን ክብርና ውርደት የሚሆንባቸውን ይጨምራል። እንደ መስፍን ገለጻ የአንድ ሕዝብን ታሪክ ለማጥናት ልማዱንም ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህም እንደ አንድ የጥበብ ሙያ በተማሪ ቤት ውስጥ በተወሰነ ጊዜ የሚማሩት ሳይሆን ኑሮ ውስጥ ተነክሮ በማደግ የሚገኝ የመንፈስም ረቂቅነት ያለው ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ፤ የጸሐፊ ማንነትም በታሪክ ቸል የማይባል ጉዳይ ነው ሲሉ ጽፈዋል። ለዛም ነው የታሪክ ባለቤት ለሆነ ሕዝብ የታሪክ ባለሙያው ፍጹም ባዕድ ሲሆን ታሪክ መወላገዱ አይቀርም የሚሉት።

ታሪክ ለምን?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተማሪ ሰለሞን ስዩም ተከታዩን ለታሪክ ትርጓሜ የሰጠ ገጠመኝ ይጠቅሳሉ። ፍሬድሪክ ኒቼ በአንድ መጽሐፉ ላይ ከበሬ ጋር በራሱ ምናብ ያወራል። ለበሬውም ብዙ ነገር ይነግረው ይነግረውና “ነገሩን እንዴት አየኸው?” ሲል ይጠይቀዋል፤ በሬውን። በሬው ግን መልስ አልሰጠውም፤ ያኔ ኒቼ “ለካ ሰው መሆን ማስታወስ ነው” አለ። እናም ማስታወስ መቻል ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ጸጋ ነው፤ ይህም በተዘዋዋሪ ለታሪክ ክብደት ይሰጠዋል።

ይህ ሐሳብ ካለፉ አገራዊ ቀውሶች የባሱ ግጭቶች በ“ታሪክ” ምክንያት ሲከሰቱ ለተመለከቱና፤ “በታሪክ የመኖር ትርጉሙ አልገባንም፤ ታሪክ ምን ይሠራልናል?” ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች ምላሽ ሳይሰጥ አይቀርም። ብዙዎችም እንደሚስማሙበት ታሪክን ያመጣው ሰው መሆን ነው። እንደ ዱላ ቅብብል ትውልድ የተበጣጠሰ ሩጫን እንዳይሮጥ፣ እየኖረም እያለፈም አሻራውን እንዲያሳርፍ የሚረዳው ታሪክ ነው።

የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ታምራት በበኩላቸውም፤ የሰው ልጅ እንደውም ከታሪክ አይላቀቅም ይላሉ። የሠራውን መጥፎም ይሁን ጥሩ ነገር አይረሳምና። የታሪክ አስፈላጊነትን በተመለከተም ኤድዋርድ ካር የተባለ የታሪክ ሰው ስለታሪክ ምንነት ከጠቀሰው ይነሳሉ፤ በዚህ መሠረት ታሪክ በማኅበረሰብ መካከል ግንኙነት የሚካሔድበት መድረክ ነው። ታሪክ አሁን ያለው ማኅበረሰብ ካለፈው በማወቅ ወይም ባለማወቅ የወረሳቸውንና የወረሰበትን መስተጋብር ያጠናል፤ በሕዝቦች መካከል የጋራ ነገር እንዲኖር መንገድ ይከፍታል። ሕዝብ ስለአገር ያለውን አመለካከትም ይቀርጻል።

እንደ ሳሙኤል አሰፋ ገለጻ ደግሞ፣ ታሪክ የአንድ ማኅበረሰብ አገራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሞራላዊ ልዕልና የሚገነባበት መሰረት እና ውሃ ልክ ነው። ዛሬ በትናንት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ሁሉ የትኛውም ማኅበረሰብ የተገነባበት ታሪክ አለው። ያለ ትናንት ዛሬ ምሉዕ አይሆንም። ታሪክ የትናንት ልማትም ሆነ ጥፋት የሚማርበት ህያው ምስክር ነው።

ለዚህም የሮበርት ፔን ዋሬንን አነጋገር እንዲህ ሲሉ ጠቅሰዋል፤ “ታሪክ የመጪውን ጊዜ መርሃ ግብር አያበረክትልንም። ይልቁንም ስለራሳቸው ማንነት እና ስለተለመዱ ስብዕናዎቻችን የተሟላ እውቀት ይሰጠናል። በዚህም እኛ መጪውን በተሻለ ሁኔታ ለመጋፈጥ እንችላለን”

ሰለሞን ተሰማ ይህን በተመለከተ በጽሑፋቸው ካሰፈሩት ስንዋስ፥ የታሪክ ዋጋው ለዘመኑ ብቻ ሳይሆን ለተከታዩም ጭምር እንደሆነ ይነግሩናል። “አንድ ሰው ከእርሱ ቀድሞ የኖሩት ወገኖቹ እነማን እንደነበሩ ምንስ እንደፈጸሙ ለማወቅ መጠበብ ሰብኣዊ ሕግ ነው።…. ታሪክ የወደ ፊት እርምጃዎችን አነሳሽና አትጊም ሆኖ እናገኘዋለን” ሲሉም ይሞግታሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታሪክ ባለሙያዎች፣ በታሪክ ዙሪያ ሥራዎችን ያቀረቡ ግለሰቦች እንዲሁም ያገላበጠቻቸው መጻሕፍት ሁሉ የታሪክ አስፈላጊነት ላይ ጥርጥርና ጥያቄ አያነሱም። እንደውም ታሪክ የነበረውን ዕድገትና እርምጃ በማሳየት ለዛሬና ለነገ አትራፊነት የሚጠቅም ስለመሆኑ በተለያየ የቃላት አደራደር ይገልጻሉ። ታድያ በአገራችን ምነው ታሪክ የግጭት ምንጭ፣ ለፖለቲካም ግብ ማስፈጸሚያ የዋለ? ለምንድን ነው ዛሬ ኢትዮጵያን አዘናግቶ ከነገ እያዘገያት ያለው?

ታሪክና ኢትዮጵያ – ከትላንት እስከ ዛሬ
ኢትዮጵያ ታሪክን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ (‘አካዳሚያዊ’) ደረጃ ማጥናት የጀመረችው ከአውሮፓና አሜሪካ በ100 ዓመታት ዘግይታ ነው። ከዚያን ጊዜ ቀደም ብለው ይጻፉና ይነገሩ የነበሩ ታሪኮች፤ የሕዝብን እሳቤ በመቅረጽ በኩል ብዙ አስተዋጽዖ ነበራቸው፤ እንደ ሰለሞን ስዩም ገለጻ። “ከዛ የተነሳ የመንግሥት ፖሊሲ ሕዝቦችን የሚያይበትን መነጽር ሰጥተውታል ማለት እንችላለን።”

ከ1960 በኋላ ዘመናዊ የታሪክ ትምህርት ዳዴ በሚልበት ጊዜ በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች በተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት እውቀት ደረጃና ልክ ታሪክን ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል ሙከራ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከመጀመሩም የግጭት መነሻ ሆኖ ነበር። እንደ ሰለሞን ስዩም ገለጻ ደግሞ፤ “የታሪክ ብያኔ ላይ እስከዛሬ ያልተፈታ ከፍተኛ ልዩነት አለን። ታሪክና ርዕዮተ ዓለም መቀላቀሉ” ሲሉ ይናገራሉ።

በተረፈ ግን ታሪክና ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም የተለየ ግንኙነት የላቸውም። ታሪክ ለተለያዩ ነገሮች መጠቀም የሚቻል ሆኖ፤ ብዙ ጦርነቶች በታሪክ የተነሳ አጋጥመዋል፤ ደርሰዋል። ታሪክ የእልቂቶች መነሻም ሆኖ ያውቃል። ለምሳሌ በአውሮፓም ብቻ በታሪክ የተነሳ ለቁጥር የሚያታክት ጦርነት ተደርገዋል ሲሉ ሰለሞን ጣልያን፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንደ ሰለሞን ስዩም ሁሉ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ ታሪክን መነሻ ያደረገ ውዝግብ በበርካታ አገራት ላይ ይታያል ሲሉ ያነሳሉ። እንደ ምሳሌም ሬድ ኢንዲያን በመባል የሚታወቁት የአሜሪካን ነባር ነዋሪዎች እና መጤዎቹን አውሮፓውያን፣ ነባር የአውስትራሊያ ነዋሪዎች (አቦርጅንስ) እና መጤ የሚባሉት ነጭ አውሮፓውያን፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እና አውሮፓውያን…ወዘተ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከየራሳቸው ምልከታ የሚጽፉት የማይታረቅ መሆኑ ለተለያዩ ግጭቶች እንደዳረጋቸው አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታሪክ ላይ ፍጅቶች ዐይን እያወጡና እየጎሉ ሔደዋል። ዘመናዊ የታሪክ ጥናት ዘግይቶ በጀመረባት አገር የሚደረገው የታሪክ ጥናት ራሱ ዛሬ ድረስ በቂ እንዳይደለ የሚናገሩት ሰለሞን ስዩም፥ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋት እያጠና የሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው ብለዋል። ይሁንና ጥንታዊውን እና የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ የሚያጠና እንደጠፋ ይገልጻሉ። “ትኩረቱ ሁሉ የቅርቡ ላይ ነው፤ ለዛውም የፖለቲካ ታሪኩ ነው የሚጠናው” ብለዋል።

ለጥንቱ እነ ሥርግው ሀብለሥላሴ፣ ለመካከለኛው ዘመን እነ ታደሰ ታምራት እንዲሁም የዘመናዊ ታሪክ መግቢያ ላይ ያለውን እነ መርዕድ ወልደአረጋይ ያጠኑት ጥናት ብቻውን ተቀምጧል። ከዚህ ጉድለት ባሻገር ታድያ እንደ ሰለሞን ስዩም ገለጻ፤ በታሪክ ላይ የማኅበረሰቡ እሴት አይታይም። በሌላ አገላለጽ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ታሪክ አልተጻፈም፤ አይጻፍም ነው።

ታምራት በበኩላቸው ከዚህ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ የታሪክ ጽሑፎች እንዲጻፉ የሚፈለግበት የጊዜ ገደብ አለ ይላሉ። በዚህም 25 ዓመት በኢትዮጵያ ነጻ የሚሆንበት ጊዜ ነው። ይህን ሐሳብ ሳይጥሉ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ሰለሞን፤ የታሪክ ምሁራን “ሦስተኛ ትውልድ” የሚሉትን እሳቤ ይጠቅሳሉ። በዚህም የታሪክ አካል የሆነ ሰው አልፎ፤ ታሪኩን ቀጥታ የወረሰ ልጅም ተተክቶ ታሪኩን መጻፍ የሚገባው ከኹለቱ በኋላ የመጣው ሦስተኛ ትውልድ ነው፤ ከታሪኩ ቅዝቃዜም ሆነ ትኩሳት ገለል ማለት ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ።

ነገር ግን አሁን ላይ የሦስተኛ ትውልድ እሳቤም ሆነ የ25 ዓመት ቆይታ ሲሠራ አይታይም። ከ25 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ታሪክ ተጽፎ ይታያል። ያም ሆነ ይህ ግን ዋናው ነገር በሥራዎቹና በሕዝቡ መካከል ሆኖ የተባለውን በቀላል ቋንቋ ሳያዛባ የሚያደርስ አካሔድ ያስፈልጋል ነው።

እንዴት ባከነ፤ እንዴትስ አዘገየ?
ጸባያቸው እያደር እንደሚገለጥ ረጅም ጉዞ እንደወጡ ወዳጃሞች፤ የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ከተዘረጋ ዓመታት በኋላ “የእኔ ነው!” ዓይነት ትርክቶች በብዛት መስማት አሰልቺ ሆኗል። በቀን ሦስት ጊዜ መብላት አጀንዳ ሆኖ በሚቀርብባት አገር ውስጥ፣ ትክክለኛነት ያልተረጋገጠ የትላንት ጸብ ካሳ እያጠያየቀ ይገኛል።
ሰለሞን ስዩም፤ የኢትዮጵያን የታሪክ አጠቃቀምና አረዳድ በተመለከተ ሲያነሱ፤ “ታሪክን ለነገ ብንጠቀም አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ትላንት ለመኖር ነው እየተጠቀምንበት ያለነው” ይላሉ። ይህም ነው ዛሬን አባክኖ ከነገ የሚያዘገይ ድርጊት። ቀደም ብሎ “ጨቋኝ” የተባለው አካል ወገን ዛሬ ላይ ሆኖ “የኔ ወገን ትክክል ነበር” ሲል ታሪክን ጠቅሶ ዛሬ ላይ “ተጨቆንኩ” የሚለውም ያለቅሳል። ይሁንና ግን ታሪክ ዕድገትና ወደ ፊት መሔድ ነው።

ታድያ በተለያየ አጋጣሚ የተዛቡ ታሪኮችን ለማስተካከል እንኳን መንገዱ ምቹ አይደለም። አንድ ጊዜ የሕዝብ ‘እውቀት’ የሆኑ ታሪኮችን ማስተካከልም ጊዜ የሚወስድ ሒደት እንደሆነ ሰለሞን ስዩም ይጠቅሳሉ። የታሪክ ጥናቶች ዳግም ምልከታ (revisit) እንደሚደረግባቸውና አልፎም አንድ ሰው ከዓመታት በፊት በሠራው ታሪክ ነክ ጥናት ዙሪያ ዛሬ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል። በታሪክ “ጨረስኩ” የሚባል ነገር የለምና። ለሰፊው ሕዝብ ከሥር ከሥር ሊነገር እንደሚገባ ግን ልብ ይሏል!
ወዲህ ደግሞ ችግሩ ሌላ ነው። አንድ የታሪክ ባለሙያ ተነስቶ አስቀድሞ እውቀት ሆኖ የተመዘገበን “ታሪክ” ሊያሻሽልና ሊያስተካክል ቢሞክር ከ“ኑፋቄ” ይቆጠርበታል፤ እንደ ሰለሞን ስዩም ገለጻ። ይህም በኢትዮጵያ ከለውጥ ጋር አብሮ የመሔድ ችግር መኖሩን ማሳያ ነው ይላሉ።

ኹለተኛውን የኢትዮጵያና ጣልያን ጦርነትን በተመለከተ ይልቁንም የሰሜን ሸዋ አርበኞች ታሪክ ላይ ጥናት በማድረግ እንዲሁም “ተከፍሎልናል” በተሰኘ ዘጋቢ ፊልም የሚታወቁት ሜላት ዳዊት፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆን ገጠመኝ አላቸው። ይህም “ተከፍሎልናል” የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም ሠርቶ ለማጠናቀቅ ያዩት አስቸጋሪ ፈተና ነው።

ታድያ ይህን ታሪክ ነክ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ለማቅረብና ለማጠናቀቅ ለአንድ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጥያቄ አቅርበው ነበር። በዚህም ሥራው ሲጠናቀቅ ለዩኒቨርስቲው የታሪክ ትምህርት ክፍል ግብዓት እንዲሆን እንደሚሰጡም ለዩኒቨርስቲውና ለትምህርት ክፍሉ ገልጸዋል። ከዩኒቨርስቲው ያገኙት መልስ ግን “እኛ የእርዳታ ድርጅት እንመስልሻለን ወይ?” የሚል ነበር። ከዚህ የከፋው ደግሞ ይኸው ተቋም በጥቂት ወራት ልዩነት ከሦስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ለአንድ ድግስ ወጪ ማድረጉ መገለጹ ነው።

ምክንያታዊ ያልሆነ እንዲህ ያለ የተቋማት ዝንጋኤ ባለው መዘናጋት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፍ መሆኑ አያጠራጥርም። እርማት በሚደረግ ጊዜም ድልድይ ሊሆኑ የሚገቡት በአግባቡ እየሠሩ አይታዩም። እናም አሁንም ታሪክን መሠረት ያደረጉና የሚጠቅሱ ጭቅጭቆች ማቆሚያቸው ቅርብ አይመስልም።

የሚያጨቃጭቀን ምንድን ነው?
ታሪክ? ተራኪ? አተራረክ? አረዳድ? የጭቅጭቁ ምንጭ እያንዳንዱና ሁሉም እንደሆኑ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ከዚህም አልፎ አንድን ኹነት በተመለከተ የተለያዩ ታሪኮች ሲነገሩ ይሰማል። አንዳንዴ ይሔ ልዩነት ከ”ወዳጅ” እና ከ”ጠላት” የሚቀርብ ነው። የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲው መምህር ታምራት ሲናገሩ፤ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ታሪኮችን የመስማታችን ምክንያት ጸሐፍቱ ከሚጠቀሟቸው መረጃዎች ነው ይላሉ። “እኛ አገር ሁሉም ሰው ይጽፋል፤ ግን ምንጩ አጠያያቂ ነው። እናም አንዱ የውዝግብ መነሻ ምንጮች ናቸው፤ የታሪክ ምንጮች”

በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ያከሉት ሰለሞን ስዩም፤ በታሪክ ስላለፈው የሰው ልጆች ድርጊት ሲጠና ሐሳብና ድርጊት እንደሚመረመር ይጠቅሳሉ። ለዚህም ግብዓት የሚሆኑ ምንጮችን መተቸት አስፈላጊ እንደሆነ ያነሳሉ። ምንጩ ምን ያህል ተዓማኒ ነው ብሎ መመርመር የሚቀድም እንጂ አንድን ጽሑፍ አንድ ግለሰብ ስለጻፈው ብቻ “እገሌ እንዳለው…” ብሎ መጥቀስ በታሪክ አይፈቀድም። እንደ ሰለሞን ገለጻ፤ “የሙሉ ጊዜ ታሪክ ምሁራን ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ላይ ማተኮር አለባቸው”
ኹለተኛው በታምራት ዕይታ ታሪክን እንዲያጨቃጭቅ መንገድ የከፈተው ጸሐፊ ነን የሚሉ ሰዎች የሚገኙበት የአስተሳሰብ ደረጃ ነው። እነዚህ ጸሐፍያን ትላንትን በዛሬ ዐይን የሚያዩ በእንግሊዘኛው “ፕረዘንት ማይንድድ” የሚባሉ ታሪክ ጸሐፍያን ናቸው። ታሪክን ሲጽፉ ራሳቸውን ያኔ ላይ ማስቀመጥ መቻል ሲኖርባቸው፤ ዛሬ ላይ ሆነው የቀደመውን በዛሬ ዐይን እያዩ የሚወቅሱ እንደማለት ናቸው።

ሌላው ያነሱት ደግሞ የጸሐፊውን ዕይታ ነው። ይህም “የቀድሞ የጋራ ታሪክ አለን” በሚሉ እና “አይ የለም! ሁሉም የየራሱ ታሪክ ነው የነበረው” በሚሉ አስተሳሰቦች መካከል ካለው ልዩነት የሚጀምር ነው። ታምራት ቀጥለው የጠቀሱት ግብን ወይም ዓላማን ነው። “አንድ ሰው አንድን ታሪክ ለመጻፍ ያነሳሳው ምክንያት ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ እዚህ ላይ ይነሳል። በዚህም የታሪክ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ ታሪኩን ከማጥናት በፊት ስለ ታሪኩ ጸሐፊ ማንነትና ስለተነሳበት ዓላማ ማወቅ ያሻል።

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ታድያ ከ1960ዎቹ ወዲህ ያሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች ላይ እንዲሁም የታሪክ አረዳድ ላይ ብልሽት መፈጠር እንደ ጀመረ ብዙዎቹ አንስተዋል። ታሪክ የሚጽፉበት ዓላማም የተለያየ ነበር። በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ከሚጻፍባቸው መዋዕለ ዜናዎች፣ ገድላት እንዲሁም የጉዞ ማስታወሻዎች ውጪ ታሪክ ጸሐፍያን በተለያየ መደብ ተከፍለው ታይተዋል።

ከእነዚህም ቀዳሚዎች በጊዜው ያለውን መንግሥትን የሚደግፉ ናቸው፤ የቤተመንግሥት ታሪክ መዝጋቢዎች፤ በእንግዚለኛው establishment Historians ይሏቸዋል።

ሌሎች ደግሞ የዘውግ ታሪክ ጸሐፊዎች ወይም Ethno Nationalist ሲባሉ፤ በእነዚህ ታሪክ ጸሐፍት ምክንያት የታሪክ ሽሚያ እንደተጀመረ ይነገራል። የታሪክ መምህሩና የ“መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ አዘጋጅ ታዬ ቦጋለ፤ በዚህ የታሪክ ጽሕፈት ዘውግ ውስጥ ያሉ ሰዎች “የእኔ ነው” የሚል ታሪክ የጀመሩ ናቸው ይላሉ።

የቀሩት ደግሞ የሰው ልጆችን ታሪክ በመደብ ትግል ፈርጀው የሚጽፉና አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርገው የሚያሰፍሩት ናቸው።
ታዋቂው ጀርመናዊ ፈላስፋ እና ምሁር ኒቼን “እያንዳንዱ ታሪክ ሌሎች ታሪኮችን ይደብቃል” የሚል አባባል የጠቀሱት ሳሙኤል፤ ታሪክ ክስተቶችን መራጭ ነው ይላሉ። በተጨማሪም የጸሐፊዎች ማንነት ማለትም ታሪክን የሚጽፈው ሰው ምልከታው ከማን አንጻር ነው የሚለው የታሪኩን ዓይነት እና ውጤቱን ይወስነዋል። ለምሳሌ አንድ ታሪክ ከሌሎች ማዕዘኖች አንጻር ቢጻፍ ውጤቱ ሌላ ሊሆን ይችላል፤ ታሪክ ከሚጻፍበት ምልከታ አንጻር ሊተረጎም ስለሚችል።

ታዬ “መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ካነሱት ነጥብ መካከል ታድያ ይኸው የታሪክ አጻጻፍ ችግር አንዱ ጥላሸት እንደሆነ ነው። በመካከልም እንዲህ የሚል ሐሳብ አስፍረዋል፤ “የአትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ቁልፍ ችግር የፖለቲካ ፍላጎት ከታሪክ ትምህርት ዓላማ በተቃረነ መልኩ መዛነቁ ስለመሆኑ በቅርብ ጊዜ ታሪክ በተዘጋጁ ሰነዶች ውስጥ በጉልህ ይታያል። በተለይ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን በተለይ ‘ታሪክን ለፖለቲካ አጀንዳ’ መጠቀም ከየትኛውም ጊዜ በላይ መርሆ ሆኖ እና ገንኖ ታይቷል። የታሪክ ዝንፈቶችም በታሪክ ቀመስ ጽሑፎች ውስጥ በገሃድ ተንጸባርቀዋል” ሲሉ አስፍረውታል።

ሰለሞን ስዩም ከዚህም መለስ ብለው ይመለከታሉ። ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረ ማግስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን ሰብስበው ያናገሩበትን መድረክ ከሽፈራው በቀለ ጽሑፍ አገኘሁት ካሉት ያስታውሳሉ። ያኔም እንደ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ያሉ የሙሉ ጊዜ የታሪክ ጸሐፍያን፤ ኢትዮጵያ በብዙ ችግር ውስጥ ነበረችና፤ እነርሱ ሥራቸውን መሥራት እንዲቀጥሉ የታሪክን ነገር ግን ለታሪክ ሰዎች እንዲተዉ ነግረዋቸው ነበር። ሰለሞን እንደሚሉትም መንግሥት ታሪክ የመበየን አቅጣጫ የማሳየት ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አልነበረበትም።

ነገር ግን መንግሥት እጁን አላሳረፈም፤ በትምህርቱ ስርዓቱ እጁ አለና ታሪክንም ከመነካካት አልቦዘነም። ይህን ችግር ሊጋፉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ የጥናት ማዕከላትም ከችግሩ ትብታብ ያመለጡ አይመስሉም። ሰለሞን እዚህ ላይ ያነሱት ይህንን ነው። የታሪክ ጥናት ማዕከላትም በብሔር ተመድበው የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የሶማሌ ታሪክ ጥናት ተብለው በየግላቸው እየሮጡ ይገኛሉ። በሰለሞን ገለጻ “ትምህርቱንም ማኅበራዊ መቧደኑ እየጎተተ እየወሰደው ነው”
የ“ተከፍሎልናል” ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ ሜላት በበኩላቸው ደግሞ በታሪክ ጸሐፍቱና በባለጉዳዩ ሕዝብ መካከል እንዲሁም በጸሐፍያኑ መካከልም ድልድይ የለም ባይ ናቸው። “ሁሉም በዘመኑ የፈለገውን እየጨመረ የሚጠቅመውን እየጣለ አንዳንዴም ከምንም እየተነሳ የሚጽፍ አለ” ይላሉ። በዛም አለ በዚህ ግን ሁሉም የሚያመለክተው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የታሪክን ጨርቅ እንዳስጣለ ነው።

ፖለቲካ እና ታሪክ
ብዙዎች ታሪክ ከፖለቲካ ጋር ያለው ዝምድና ለዚህ እንዳበቃው የሚናገሩ ናቸው። እንደ ሰለሞን ስዩም ገለጻ፤ ከ1960ዎቹ ጀምሮ፤ ታሪክ ለፖለቲካ እንደ ጥሬ ግብዓት ነው ማለት ይቻላል። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የተለየ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የበርካቶቹ የዓለም አገራት ታሪክ ከፖለቲካ ታሪክ የሚጀምር ነው። ምክንያቱ ደግሞ ቤተመንግሥታት መካነ እውቀት በነበሩ ዘመን ጽሕፈትም የጀመረው ከዛ በመሆኑ ነው።

ሳሙኤል እንዳሉት ደግሞ ለታሪካችን ቅቡልነት ማጣት በራሱ ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል እንደ ዋና ምክንያት ሊቀመጥ ይችላል። በአንዳንድ ወገኖች ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የነዛው የብሔር ጭቆና ፕሮፓጋንዳ፤ እንዲሁም የማርክሲስታዊ የታሪክ አጻጻፍ እና አተረጓጎም በጨቋኝ መሪዎች እና በተጨቋኝ ሕዝብ መካከል የነበረውን የመደብ ጭቆና ወደ ብሔር ጭቆና አቅጣጫ ማስቀየሩ ዋልታ ረገጥ የሆኑ የታሪክ አጻጻፍ እና አረዳዶችን የወለደ ይመስላል፤ እንደ ሳሙኤል ገለጻ።

ሳሙኤል እዚህ ላይ የታዬ ቦጋለን መጽሐፍ ይጠቅሳሉ። በዚህም መሰረት በአንድ በኩል የገዢው መደብ ታሪክ ጸሐፊያን ነገሥታትን ልዕለ ሰብዕ አርገው መመልከታቸው፤ በሌላም መልኩ ደግሞ የዘውጋዊ ፖለቲካ ልኂቃን የእኛ እና የእነሱ በሚል በፈጠሩት ክፍፍል የእኛ የሚሉት ወገን ደግ እና ሩህሩህ የእነሱ የሚሉት ደግሞ ጨካኝ እና ክፉ አደርገው መሳላቸው በታሪክ ላይ ለተፈጠረው ክፍፍል ዋና ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።

ማን የማን እስረኛ?
ፖለቲካና ታሪክ በአንድም በሌላም መልኩ በታሪካቸው የሚገናኙ ከሆኑ፤ ግንኙነታቸው ሊኖረው የሚችለው መልክ አለ፤ ወይ ይተባበራሉ አልያም ይገፋፋሉ። የሚገርመው ታድያ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ አንዱ የሌላው እስረኛ ሆነው ይታያሉ። ለአንዱ ጥቅም ሲባል አንዱ ያጎነብሳል፤ አንዱ እንዲያሸንፍ ሌላው ዝቅ ይላል።

ሰለሞን ስዩም በመጀመሪያ የሰው ልጅ ራሱ የራሱ ታሪክ እስረኛ ነው ይላሉ። ታሪክ ደግሞ የፖለቲካ እስረኛ። ይህ እንዲሆን ያደረገው አንድም የማኅበራዊ ሚድያው አብዩት ነው። እዚህ ላይ ሽፈራው የጻፉትን የሚጠቅሱት ሰለሞን፤ በቀደመው ጊዜ የነበሩ የታሪክ ጸሐፍት ሲናገሩ በደርግና በቀደመው ጊዜ መንግሥት ጫና ለማድረግ ሞከረ እንጂ አልተሳካለትም ነበር። የታሪክ ጸሐፍቱም “እኛ በታሪክ መመዘኛ መሰረት ነው የሠራነው፤ አላጎበደድንም” ሲሉ ይሟገታሉ። ይህም ታሪክ ለፖለቲካ እስረኛ ከሆነ እንዳልቆየ ያሳየናል።

አሁን ላይ ግን በተለይ ማኅበራዊ ሚድያው ታሪክን እስረኛ እንዳደረገው ነው የሚጠቀሰው። ሰለሞንም ይህን ሐሳብ ይዘው ማኅበራዊ ሚድያውን ሲታዘቡ፤ ብሔራቸውን እየጠሩ “ንጹሕ…. ነኝ” የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ይህ ግን ፍጹም ታሪክ አለማወቅን የሚያሳብቅ እንደሆነና የኢትዮጵያን መካከለኛ ዘመን ታሪክን ለተመለከተ “ንጹሕ እንትን ነኝ” የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል ይጠቅሳሉ።

ሜላትም በበኩላቸው “ታሪካችን የፖለቲካ እስረኛ ነው ብዬ አምናለሁ” ይላሉ። ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ጀብዱ በሚመሰክሩ ሰዓት የታሪኩ ባለቤቶች ግን በታሪኩ ላይ ሲነታረኩ ከታየ፤ የመታው መንግሥት ሁሉ እያደበዘዘው ሊያልፍ የሚፈልገው አንዱ ነገር ታሪክ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

የታሪክ ባለሙያዎች ታድያ አሁን ላይ የት አሉ ሲባል፤ ሳሙኤል እንደጠቀሱት፤ እንዳለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ የታሪክ ብያኔ እየተሰጠ ያለውና የሚሰጠው በባለሙያዎች ሳይሆን በፖለቲከኞች ነው። ፖለቲከኞች በፖለቲካ መነጽር እና በወገንተኝነት በተቃኘ ብያኔ የሚሰጡት የታሪክ ትርጓሜ ሕዝብን ከፋፍሎ አገር በዴሞክራሲ እና ኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንድትቀር አድርጓታል።

በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁራን አሉ። በእነዚህ ባለሙያዎች የተዘጋጁ የታሪክ መጻሕፍትን ለንባብ የሚያቀርቡ የጥናት ማዕከላትም እንደዛው። ነገር ግን መኖራቸውን የሚያውቁና መኖራቸው የተሰማቸው ብዙዎች ናቸው ለማለት አይደፈርም። ምን ያህል ሰው አንባቢ ነው፤ መጽሐፍቱስ ምን ያህል ተደራሽ ናቸው፤ መገናኛ ብዙኀንስ ድርሻቸውን ተወጥተዋል ወይ? የሚሉጥ ጥያቄ ሆነው ይቆያሉ።

በእርግጥ የታሪክ ምሁራን ምን ያህል ናቸው ቢባልና በጥልቀት ቢታይም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ አይቀርም። ለምን ቢባል፤ ሰለሞን ስዩም እንዳሉት፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ታሪክን ለማጥናት የሚሰጡ ናቸው ይህን መስፈርት ሊያሟሉ የሚችሉት። ታሪክ ደግሞ የመንግሥትም የሕዝብም ድርሻ አይደለም፤ የታሪክ ባለሙያው እንጂ።
“የኢትዮጵያ ታሪክ ትርክትና ታሪካችን” የተሰኘውን መጽሐፍ እዚህ ላይ የሚጠቅሱት ሳሙኤል፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ ግዛው ዘውዴ በታሪክ ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን ለመፍታት ትርጉም፣ የአተናተን ዘዴና የድምዳሜ ተፋልሶ በታሪክ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎችም ላይ የሚስተዋል ነው ይላሉ። የታሪክ ምሁሩ ግዛው በታሪክ ላይ የሚነሱ ስምምነት ማጣቶች ምክንያቱ ትረካው በማስረጃ ያለመሟላቱ የጥናቱ ሥነ ዘዴ (Methodology) የዘርፉን ዲሲፕሊን ሳይጠብቅ ከምሁራዊ ስክነትና ሆደ ሰፊነት ይልቅ ጨፋሪ ስሜታዊነት ያጠላበት በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም እኚህ የታሪክ ምሁር “በመሰረቱ ታሪክ ፖለቲካዊ ቅርጽ ከመስጠት ይልቅ ትምህርታዊ እና ሙያዊ ጠገጉን በጠበቀ መልኩ ቢከናወን ኖሮ እያረሙና እያስተካከሉ ማስቀጠል አይቸግርም ነበር” ይላሉ።
ታሪክን መጻፍና መተንተን ያለበት የታሪክ ተመራማሪ ብቻ ሳይሆን አንትሮፕሎጂስቶች፣ ሶስይሎጂስቶች ወይም የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁሮችና ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው። እነዚህ ነገሮች የተያያዙ ስለሆነ ሁሉም የተለያየ ዘዴ ቢጠቀሙም መጨረሻ ላይ የሚያገናኛቸው ነገር፤ የማንኛውም ማኅበረሰብ ሒደት አንድ ሕዝብ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ የሚተረጎም ስለሚሆን ነው።

እንደሚታወቀው አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ የብዙ ዓመታትን ምርምርና ጥናት ስለሚጠይቅ ማንም እየተነሳ ስለ አንድ አገር ታሪክ በፈለገው መልክ ሊናገርና ሊጽፍ አይችልም። ስለሆነም ማንኛውንም ዕውቀት ለባለሙያዎች መተው ከብዙ ጭቅጭቅ ያድነናል። የታሪክ ትርጓሜ ሳይንሳዊ ሒደትን መከተል ያለበት እንጂ በዘፈቀደ የሚደረግ ስላልሆነ ነው።

መስፍን ወልደማርያም በዚሁ ሐሳብ ዙሪያ መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ “የታሪክ ባለሙያዎች ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተረት የሚሉትንና ታሪክ የሚሉትን አጣርተው ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው እንጂ በቋንቋም ሆነ በማናቸውም ባሕል ባዕድ የሆኑ ፈረንጆች ለራሳቸው ዓላማ የሚወረውሩትን ሁሉ እየለቀሙ ያልተማሩትን ፈረንጆች በማስተማር ላይ ማተኮር ኢትዮጵያን ቅንጣት ያህል እንዳልረዳ ያልተገነዘበ መንቃት አለበት” ሲሉ፤ አክለውም በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ውስጥ ብዙ እንቆቅልሾች አሉ፤ ነገር ግን የታሪክ ምሁራን አንዱንም ተጋፍጠው በጥልቀት ለማጥናትና እንቆቅልሹን ለመፍታት እስከዛሬ አልሞከሩም ሲሉ ይገልጻሉ።

ምን ይበጃል?
ልብወለድና ድርሰት ሥራዎች ከደራሲው እጅ ከወጡ ወይም ተደራሲው እጅ ከገቡ በኋላ የድርሰቱ ሙሉ ባለመብት ተደራሲ ወይም አንባቢ ነው። እንደውም ደራሲው በዛ ጽሑፍ ፊት ሞቷል ነው የሚባለው። ተደራሲ በፈለገውና በገባው እንዲሁም በቆመበት ጫማ ልክ መተርጎምና መረዳት ይችላል። ወዲህ ታሪክ ግን እንደዛ አይደለም። አንድ ሥራ እንደዛ ዓይነት ሐሳብ ካቀበለ ታሪክ ሳይሆን ልብ ወለድ ሆኖ መመዝገቡ አይቀሬ ነው። ጥፋቱም አንድ ደራሲን “ቀሽም ድርሰት” ብሎ ከመውቀስ የሚያልፍ፤ በአገር ሕልውና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው።

ታድያ ብዙዎች የሚናገሩት ኢትዮጵያ ትርክቶቿን በማስተካከል ብዙ ችግሮቿን ማስተካከል እንደምትችል ነው። የመፍትሔ ሐሳብ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ ያቀበሉት ሰለሞን ስዩም በበኩላቸው፤ ታሪክን ያመጣው ማስታወስ መቻል የሚባለው የሰውነት ከፍታ በመሆኑ እንዲሁም በጭራሽ ያለ ታሪክ መኖር አይቻልምና፤ “ይህን ልዩ ያደረገንን ስጦታ ከፍ ባለ ደረጃ ልንኖርለት ይገባል” ባይ ናቸው።

ይህን ከመረዳት ባሻገር ታሪክ ሳይዛባ እንዲደርስ የሚያስችል መደበኛ መገናኛ ብዙኀን አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። “የእኛ አገር ጋዜጠኞች ያለማንበብ በጣም ችግር አለባቸው። በአንጻሩ ጋዜጠኝነት ትልቅ ሥራ የሠሩ እንደ ጳውሎስ ኞኞ የታሪክ መጽሐፍ ያዘጋጁም አሉ” ሲሉ ያነሳሉ።

የታሪክ መምህሩ ታምራት ደግሞ ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ ያደረሷት አሻሚ የሆኑ የታሪክ ጉዳዮች የሚታወቁ በመሆናቸው አሁን ያሉ የታሪክ ባለሙያዎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊነጋገሩበት ይገባል ብለዋል። “እውነታን በመሸሽ መፍትሔ አይገኝም፤ መጋፈጥ ይገባል” ሲሉም ይገልጻሉ።

ሌላው መፍትሔ ይሆናል ያሉት የአርትኦት (ኤዲቶርያል) ቦርድ ማቋቋምን ነው። ሁሉም በራሱ ለፈለገው ዓላማና በፈለገው መንገድ እየጻፈ ለተደራሲ እንዳያቀርብ፤ ቀድሞ የታሪክ ሥራዎችን የሚመለከት፤ ሙያዊ አስተያየት የሚሰጥ ቦርድ ያስፈልጋል። ከዚህ ባለፈ ግን ባለፈው ታሪክ ላይ አሁን መጠቀም የሚፈልጉ፤ ትላንት “ሆኗል” ለተባለው ዛሬ ካሳ የሚጠይቁ፤ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን የሚጠቅሙ እንደማይሆኑና፤ እነርሱንም የሚጠይቅ ሌላ ተከትሎ እንደሚመጣ ይጠቅሳሉ። እናም የማያልቅ አዙሪት ውስጥ እንደመግባት ይሆናል።

ይህ ግን በቀደመው ጊዜ የተከሰተ መጥፎ ትዝታዎችን እርግፍ አድርጎ መተው ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ይልቁንም የቀደሙ መጥፎ ታሪኮች የሕዝቡ አንድ አካል በመሆናቸው ለምሳሌ እንደ ቀይ ሽብር ዓይነት ክስተቶች በሰማዕታት መታሰቢያ “ከዚህ በኋላ አይደገምም” ዓይነት ቃል የሚገባባቸው ሊሆኑ ይገባል። ታምራት እንደሚሉት በጎ ላይ ማተኮር ነገ የሚያደርስ ዛሬንም የማያባክን ነው።

ሜላት በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ታሪኩን ለማወቅ፣ ጀግኖችን ለማክበርና ለማሳወቅ የሚጥሩ ወጣቶች በብዛት አሉ። ነገር ግን ድጋፍ እና ማበረታቻ ሲደረግላቸው እንደማይታይ ያነሳሉ። እናም ይህ እንዲስተካከል አበክረው ያሳስባሉ። በተረፈ ግን ከቤተሰብ ጀምሮ ለልጆች ታሪክን በአግባቡ በማሳወቅ ከማሳደግ ጀምሮ በንባብ በማበልጸግ ሁሉም በየግሉ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ሁሉም የሚስማሙበት ሐሳብ አንድ ነው፤ ይህም ቀድሞ ያለው ላይ የጋራ ነገር ፈጥሮ መቀጠል እንደሚሻል። ለዚህም ከመገናኛ ብዙኀን ጀምሮ የታሪክ ባለሙያዎችና እያንዳንዱ ግለሰብ ኀላፊነት እንዳለበት። “ታሪክ ወደኋላ ብቻ ሳይሆን የነገን የሚያመላክት ነው፤ በትላንት ላይ እየቆዘሙ መኖር ብዙ አያስኬድምና ከዚህ መውጣት ያስፈልጋል” እንደ ታምራት ገለጻ።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here