ምክር ቤቱ በሸገር ከተማ እየፈረሱ ስላሉ መስጂዶች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጻፈ

0
866

አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በቅርቡ በአዲስ መልክ “ሸገር ከተማ” ተብሎ በተመሠረተው ከተማ፤ እየተከናወነ የሚገኘው የመስጂድ ፈረሳ “አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው” የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጽፏል።

ምክር ቤቱ በደብዳቤው፤ በከተማ አስተዳደሩ “ህገወጥ” በሚል በርካታ መስጂዶች እየፈረሱበት እንደሚገኙና፣ በጉዳዩ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጋር በስልክ በመነጋገር መፍትሄ ላይ ደርሶ እንደነበር ገልጾ፤ ነገር ግን <<የከተማ አስተዳደሩ ግን በረመዳን ወር ለጊዜው የመስጂዶች ፈረሳውን እንዲቆም በማድረግ ከረመዳን በኋላ የመስጅዶች ፈረሳ በአዲስ መልከ በብዛት ቀጥሏል።>> ብሏል።

በመሆኑም የመስጅዶ ፈረሳ ጉዳይ በከተማ አስተዳደሩ “ህገ ወጥ” ስለተባለ ብቻ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን፤ የህዝበ ሙስሊሙ የኃይማኖት ዋነኛ ህልውና መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲቆም ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ደብዳቤ መጻፉን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ ነገር ግን እስካሁን ለደብዳቤው ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ በስልክ ለመነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም አለመሳካቱን የገለጸው ምክር ቤቱ፤ ለክልሉ ፕሬዝደንት ደብዳቤ ከጻፈና በጉዳዩ ላይ በአካል በመገናኘት ለመነጋገር ቀጠሮ እየጠበቀ ባለበት ወቅት፤ ተጨማሪ መስጅዶች የማፍረስ ተግባሩ መቀጠሉ፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱን አመራር እንዲሁም ሕዝበ ሙስሊሙም በእጅጉ ማሳዘኑን ገልጿል።

ስለሆነም <<ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርና እንደ የብልጽግና ፓርቲ መሪነታቸው፣ ለመስጂዶች ፈረሳ ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ የመስጠት ሙሉ ስልጣኑ እንዳላቸው በማመን ለችግሩ የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጠው>> ጠቅላይ ምክር ቤቱ በደብዳቤው ጠይቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here