የሕዳሴው ግድብ የሩብ ዓመት የቦንድ ሺያጭ በ 30 ሚሊዮን ብር ቀነሰ

0
661

ከተዋጣው 13 ቢሊዮን ብር ውስጥ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መመለስ ተችሏል

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተሰበሰበው 168 ሚሊዮን ብር መዋጮ ካለፈው ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ30 ሚሊዮን ብር ዝቅ ያለ ሆኖ ተመዘገበ።

በበጀት ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ በይፋ ከተበሰረበት መጋቢት 24/ 2003 ጀምሮ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የተሰበሰበው 13 ቢሊዮን እንደሆነ እና ከዚህ ውስጥ የመክፈያ ጊዜው ደርሶ ስድስት ቢሊዮን ብር መከፈሉን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።
የግድቡን ግንባታ ወጪ ለመሸፈን ታስቦ ለሕዝብ ሲቀርብ፣ ይህ የቦንድ ሽያጭ በ2010 ከነበረበት 2.14 ቢሊዮን ብር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሽቆልቆል በ2011 በጀት ዓመት 970 ሚሊዮን ብር ብቻ ሆኖም ተመዝግቧል።

ከሕዝብ ከሚደረገው ተሳትፎ ከመንግሥት ሠራተኞች የሚገኘው ገንዘብ ከፍተኛ ሲሆን፣ በተለይም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የፌደራል ፖሊሰ ፤የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ሎሎች የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ከ 5 እስከ 7 ዙር የቦንድ ግዢ በማካሄድ ቀዳሚ ናቸው።
‹‹የቦንድ ግዢው ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ ይሁንና የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የቦንድ ግዢ የሚቀዘቅዝበት ወቅት ሲሆን ለዚህ ምክንያቱም ደግሞ የቦንድ መክፈያ ጊዜያቸው የሚጨርሱበት ጊዜ በመሆኑ ነው›› ሲሉ የግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሚዲያ አስተባባሪ አቶ ኀይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ‹‹በ2011 ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ የተፈፀመ ሲሆን ይህም የያዝነው ዓመት እቅድም እንደሚሳካ ያሳየል›› ሲሉም ገልፀዋል።

በግድቡ ስምንት የግንባታ ዓመታት ውስጥ ከ 98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ከሕዝብ ተሳትፎ 13 ቢሊዮን ብር ብቻ ተሸፍኗል። ከግድቡ የግንባታ ወጪ ውስጥ 80 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት ቀሪው ከሕዝብ በሚገኝ መዋጮ ይሸፈናል የሚል እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ከወጣው ወጪ ግን 13.5 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው ከሕዝብ ማሰባሰብ የተቻለው። ኃይሉ እንደሚሉት ኅብረተሰቡ ላለፉት ዓመታት ባለው አቅም ሲሳተፍ መቆየቱ የሚበረታታ ቢሆንም የግድቡ ባለቤትነት በሕዝቡ ውስጥ እንዲያድር ማድረግ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ድጋፍ በሚመለከት ከመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ በዓይነት ድጋፎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ ለሦስተኛ ጊዜ ዘመናዊ የመኪና ስጦታ ለማስረከብ መቃረባቸውን እና ጽሕፈት ቤቱ ለመረከብ መቃረቡን ኃይሉ ተናግረዋል።

በክልሎች የጸጥታ እጦት ችግሮች፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ሰፊ ቅስቀሳ አለመካሄዱ፤ የህዳሴ ማስተባበሪያ ምክር ቤት አደረጃጀት አነስተኛ የሰው ኀይል ያለው፣ ከደሞዝና መዋቅር ጋር ተይይዞ በተለይም በክልል ያሉ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች የሚገባቸውን ያህል አለመንቀሳቀሳቸውም ከሕዝብ የሚሰበሰበው መዋጮ ስኬታማ መሆን እንዳይችል ማድረጉን ይገልጻሉ።

የመክፈያ ጊዜአቸው የደረሱ ቦንዶች ክፍያ በብሔራዊ ባንክ፤ በንግድ ባንክ እንዲሁም ቦንድ በሚሸጡ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል እየተፈጸመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ወላጆቻቸውን ያጡ በቤተሰቦች ከፍርድ ቤት በሚያመጡት ማረጋገጫ መሰረት የቦንድ ክፍያቸውን መቀበል ይችላሉ ያሉት ኀይሉ፣ ዜጎች አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የፖለቲካ ሁኔታ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ 68 በመቶ የደረሰ ሲሆን ከ 2 ዓመት በኋላ ኀይል የማመንጨት ሥራውን እንደሚጀምር ይጠበቃል። ግድቡ በ2016 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሆኖ ግንባታውን በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ የእስከ አሁኑን ጨምሮ ከ 130 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here