ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተለያዩ ችግሮች ከመኖሪያ ሥፍራቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
አዲስ ማለዳ ከሥፍራው ባገኘቸው መረጃ መሠረት ነዋሪዎቹ በተለይም ጃርቴ፣ አሙሩ እና ሰቀላ ከሚባሉ ወረዳዎች በብዛት የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊነት የሚገኙት በሻምቡ ከተማ ነው፡፡
በአካባቢው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው እና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በመባል በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ኃይል እንዲሁም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለረጅም ጊዜ በሚያደርጉት ውጊያ ምክንያት ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም ሳቢያ በርካታ ንጹሐን ሕይወታቸው እንዳለፈና ንብረታቸው እንደወደመ ነው የተጠቆመው፡፡
አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ በአካባቢው ከባድ የተኩስ ልውውጥ መኖሩ ጠቅሰው፤ በዚሁ ስጋት በየዕለቱ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከሆሮ ጉድሩ ዞን የሚፈናቀሉ ሰዎች ወደ ሻምቡ ከተማ ከመግባት በተጨማሪ አንጻራዊ ሠላም ወዳለበት ነቀምቴ እና ሌሎች ቦታዎች የሄዱትም በርካቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች እስካሁን አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራ አለመጀመራቸው ተገልጿል፡፡
ተፈናቃዮቹ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ምግባረ ሰናይ ተቋማት በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለተለያዩ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች እየተጋለጡ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ቀደም ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው መልሰን አቋቁመናል በማለት በዞኑ አመራር በኩል የተነገረ ቢሆንም፤ የተፈናቃዮች ቁጥር ግን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱ ነው የተገለጸው፡፡
በወለጋ በተለያዩ ሥፍራዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው ታጣቂ ኃይል መካከል ሲደረጉ የቆዩ ውጊያዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ተብሏል፡፡



