ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግብር ክፍያን እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ መክፈል እንደሚቻል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዘገየ በላይነህ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን በተለምዶ የጣራና ግድግዳ የቤት ግብር በመደበኛነት መከፈል የነበረበት እስከ የካቲት ሰላሳ ድረስ ቢሆንም፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግብር አዲስ የተጀመረ በመሆኑ ነዋሪዎች ጉዳያቸውን በማስረዳት እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ መክፈል የሚችሉ ይሆናል።
ግብር ከፋዮች እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው በየቅርንጫፉ በሚስተናገዱበት ወረዳ መመሪያ ተቀምጧል ያሉት ዘገየ፤ በመሆኑም ግብር ከፋዮቹ እስካሁን ያልከፈሉበትን ምክንያት በማቅረብ እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ ብቻ መክፈል እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
የከተማ ቦታና ቤት ግብር አከፋፈሉ የግልና የንግድ በሚል ልዩነት ቢኖረውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በከተማ ውስጥ ያሉ ከመኖሪያ እስከ ህንጻዎች ድረስ ያሉ ቤቶችን በሙሉ የሚመለከት መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
ግብሩ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ከ1937 ጀምሮ ሲሆን፤ በ1968 ማስተካከያ የተደረገበትና የኪራይ ተመኑ በየግዜው ወቅታዊ እንደሚደረግም አዋጁ ሲወጣ መደንገጉንም አስታውሰዋል።
በመሆኑም አዋጁ ሲወጣ እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያልነበሩ በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው ኪራይ ምን ይመስላል የሚለውንም በማጥናት ከተማ ውስጥ ያሉ ቤቶች ወደ ግብር ስርዓቱ እንዲገቡ በአዋጁ መካተታቸውን ጠቁመዋል።



