1-ከሰባት ወር በፊት በጊቤ ሸለቆ የሞቱት ከ30 በላይ ጉማሬዎች በአካባቢዉ ነዋሪዎች ተመርዘው መገደላቸው በጥናት ተረጋገጠ። ሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም በጊቤ ሸለቆ ከ30 በላይ የሚሆኑ ጉማሬዎች መሞታቸዉን ያስታወሰው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢዉ ነዋሪዎች ተመርዘዉ እንደተገደሉ በጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል። በተጨማሪም በካፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት አምስት አጋዘኖች ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። (ኢትዮ ኤፍኤም 107.8)
……………………………………………………………..
2- ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ነዳጅ መሸጥ እንድትጀመር ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቀዉ ኹለቱን አገራት የሚያገናኘውን የነዳጅ ቧንቧ መስመር ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ታውቋል። ግንባታው በቻይና ፖሊ ጂሲ ኤል ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የኹለቱ አገራት ስምምነት ባለፈው ቅዳሜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ በቀጣይ ሳምንታት ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
3-በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አሜሪካ ጥቅምት 26/2012 ባወያየችበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ምን እንደሚያደርግላትና ከዓባይ ውኃ ይልቅ ሌላ የኃይል አማራጭ ለምን እንዳልተጠቀመች ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተገለጸ። ለኢትዮጵያ ያቀረቡዋቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ኢትዮጵያ ግድቡ ምን ያደርግላታል?” የሚል ጥያቄ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አንስተው እንደነበር፣ ከዚህ በተጨማሪም የዓባይን ውኃ ከመጠቀም ይልቅ “አትዮጵያ ለምን ሌላ የኃይል አማራጭ አትጠቀምም?” የሚል ጥያቄም አንስተው እንደነበር ገልጸዋል። (ሪፖርተር)
……………………………………………………………..
4- የአማራ ክልል ምክር ቤት እያካሔደ ባለው 14ኛ በመደበኛ ጉባዔ ጥረት ኮርፖሬት ተጠሪነቱ ለክልል ምክር ቤት እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል። የክልሉ ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አስተዳደር ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ ሰጤ እንደገለጹት ጥረት ኮርፖሬት የክልሉ ሕዝብ ሃብት ሲሆን የአሰራር ግልፀኝነት ችግር የነበረበት ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ 11 ሺሕ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ኮርፖሬቱ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት ቢሆን ከዚህ የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችልም ተናግረዋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………..
5- በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች አዳዲስ የተመደቡ ተማሪዎች በሙሉ ተመዝግበው መደበኛ የመማር ማስተማሩ ተግባር በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ። ይሁን እንጂ በቅርቡ የትግራይ ክልል ተወላጆች በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ እንዳይመዘገቡ በመደረጋቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተማሪዎች እስካሁን አለመመዝገባቸው ይታወቃል። ነገር ግን ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች በሙሉ ገብተው እና አስፈላጊውን የምዝገባ ሂደት አጠናቅቀው መደበኛውን የትምህርት ፕሮግራም እየተከታተሉ ነው ብሏል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
6-የዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ልማት የሚውል 74 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ለግሷል። የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው ብሔራዊ ፓርኩን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማልማት እና ለመንከባከብ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።ከጥቂት ወራት በፊት በፓርኩ ውስጥ ሰደድ እሳት መነሳቱን ተከትሎ ከ400 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው የፓርኩ አካል ላይ ቃጠሎ የደረሰበት መሆኑ ይታወሳል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
7-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ሊቀ መናብርት አንዷ የሆኑትን ሜሊንዳ ጌትስን ኅዳር 1/2012 በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። ፋውንዴሽኑ የመንግሥት ዐበይት የትኩረት መስኮች ላይ አስተዋጽኦ በሚያደርግባቸው መንገዶች ላይ ምክክር አድርገዋል። ፋውንዴሽኑ ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነቷ እንዲጨምር እና ሰፊ የጤና ሽፋን እንዲኖራት ለበርካታ ዓመታት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል። (አዲስ ማለዳ)



