ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ለመመስረት በዎላይታ ዞን የተካሄደውን ኹለተኛ ዙር የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ ድምጽ አጠቃላይ ውጤት ሰኔ 19/2015 ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ትናንት ሰኔ 12/2015 በዎላይታ ዞን የተካሄደውን ኹለተኛ ዙር የሕዝበ ውሣኔ ምርጫ መጠናቀቅ አስመልክቶ ማምሻውን ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ በወላይታ ዞን በተካሄደው ድጋሚ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ የመራጮች ተሳትፎ የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ ኹሉም የምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ የምርጫ ሂደቱን ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የመምረጥ ዕድል ላላገኙ መራጮች 12 ሰዓት ላይ መጠናቀቅ የነበረበትን የምርጫ ሂደት ወደ አንድ ሰዓት ቦርዱ ማራዘሙን ተናግረዋል።
በመሆኑም እስከ አንድ ሰዓት ከ20 ድረስ በምርጫ ጣቢያዎች መገኘት የቻሉ ኹሉም መራጮች ድምፅ ሳይሰጡ አለመመለሳቸውን ገልጸዋል።
ጣቢያዎቹ ወደ ድምፅ ቆጠራ ሂደት የገቡ ሲሆን፤ እስከ ዛሬ ጧት ድረስ ቆጠራው የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ቦርዱ በ12 ማዕከላት እና በ1 ሺሕ 812 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ 9 ሺሕ 60 የምርጫ አስፈፃሚዎችን መድቦ መንቀሳቀሱን ያስታወቁት ሰብሳቢዋ፤ “በኹሉም የምርጫ ጣቢያዎች ከአስፈፃሚዎች ጋር ተያይዞ የቀረበ ችግር የለም።” ሲሉ ገልጸዋል።
ቦርዱ ምርጫውን ለምታዘቡ ለ2 የአገር ውስጥ ተቋማትና ለ206 ታዛቢዎች እውቅና በመስጠት ከእነዚህ ውስጥ 168 ታዛቢዎችን በዞኑ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ማሰማራቱን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን 7 የሰብዓዊ መብት ተከታታዮችን ማሰማራቱም ተገልጿል።
ሰብሳቢዋ መራጮች ለ6 ወር በአካባቢው መቆየታቸውን የማያሳይ መታወቂያ ይዘው መገኘታቸው፣ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ መራጮች መታወቂያ ይዘው መገኘታቸው፣ በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ድልቦአውጥሮ 1 የምርጫ ጣቢያ ላይ አንድ ግለሰብ ባዶ መታወቂያ ከቀበሌ አውጥቶ ሲሞላ እጅ ከፍንጅ መያዙን ገልጸዋል።
በተጨማሪም፤ በሁምቦ ምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚ ሳይሆን የሌላ ሰው ባጅ አንጠልጥሎ በክትትል መያዙን እና በገሱባ ምርጫ ጣቢያ ላይ ስርዝ ድል ያለበት መታወቂያ ይዞ የተገኘ ግለሰብ መኖራቸው በሕዝበ ውሳኔው የምርጫ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን በምስክርና ተጨማሪ ሰነድ እንዲያቀርቡ በማድረግ ችግሩ ተፈትቶ ድምፅ መስጠታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ እጅ ከፍንጅ የተያዙ አካላት ደግሞ ወደ ፖሊስ መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
እስከቀኑ 8 ሰዓት ድረስ 514 ሺሕ 620 መራጮች መሳተፋቸውንም ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው ማስታወቃቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።
በጣቢያዎቹ የሚከናወነው የድምጽ ቆጠራ እንደተጠናቀቀም በየምርጫ ጣቢያው ጊዜያዊ ውጤት የሚለጠፍ ሲሆን፤ በመቀጠልም የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ወደ ዞን ማስተባበሪያ ቢሮ ተሰብስበው የውጤት ማዳመር ተሰርቶ ጊዜያዊ ውጤት በዞን ደረጃ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ቦርዱ ሰኔ 19 ላይ አጠቃላይ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ከተቻለም ከተገለጸው ቀን ቀደም ብሎ ውጤት ለመግለፅ ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።



