ለአምስት የውጭ አገር ባንኮች ፈቃድ ሊሰጥ መሆኑ ተገለጸ

0
461

ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) አምስት የውጭ አገር ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎን የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የባንኩ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ ሠለሞን ደስታ ለኢፕድ ገልጸዋል።

‹‹ሥራውን አሁን እያጠናቀቅን ነው፡፡ አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው:: ከለጋሾች አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው:: በወራት ዕድሜ ለህዝብ እንደራሴዎች ይቀርባል:: ስለዚህ ሥራው እየተፋጠነ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም የገለጹት ምክትል ገዥው፤ የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን ከገበያ እንዳያስወጧቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም የተቀመጠ አሰራር መኖሩን አመልክተዋል::

ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ኹለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉትና፤ ይህም ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ መሆኑን በመግለጽ፤ አሁንም ድረስ በዚሁ አግባብ ክትትል እንደሚደረግ ሠለሞን ጨምረው አስረድተዋል::

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here