በአሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ለወራት ዝግ የነበረው መንገድ ቢከፈትም የመሠረታዊ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ

0
276

ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለአራት ወራት ተቋርጦ የነበረው ምዕራብ ወለጋ ዞን እና ካማሺ ዞንን የሚያገናኘው መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት ቢጀመርም፣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ኹለቱን ዞኖች የሚያገናኘው መንገድ ከተዘጋ ከአራት ወራት በኋላ ባለፈው አርብ ሰኔ 09/2015 ተከፍቶ የትንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ፤ የተለያዩ ምርቶች ወደ ዞኖቹ እየገቡ ቢሆንም የዋጋ ንረቱ ተባብሷል ነው የተባለው።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ነዋሪ ብርሀኑ ቶሌራ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ መንገዱ ቢከፈትም በመሠረታ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተደረገው ጭማሪ እጅግ ከፍተኛ እና ከነዋሪው የመግዛት አቅም በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ከዋጋው ጭማሪ ባለፈ ከፍተኛ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሸጌ ያሚ፤ በከተማዋ እንደ ሽንኩርት እና ቲማቲም ያሉ የአትክልት ምርቶች በኪሎ ከ100 ብር በላይ እንደሚሸጡ ጠቅሰው፣ በዚህም ዋጋ ቢሆን ምርቶችን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአካባቢው ጤፍ በኩንታል ከ10 ሺሕ ብር በላይ እንደሚሸጥ የተገለጸ ሲሆን፤ እንደ ባቄላ፣ ሽምብራ እና ስንዴ የመሳሰሉ የእህል ምርቶች በኩንታል ከ7 እስከ 8 ሺሕ ብር እንደሚሸጡ ተመላክቷል።

ይህም ሆኖ ምርቶችንና የሸቀጣ ሸቀጥ ዕቃዎችን ማግኘት በበቂ ሁኔታ ማግኘት አልቻልንም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ “ማህበረሱቡ ከፍተኛ መማረር ውስጥ ነው።” ብለዋል።

መንገዱ ተከፍቶ የመሰረታዊ ፍጆታዎች መግባት ቢጀምሩም በንግድ ሥርዓቱ ላይ በቂ የሆነ የመንግሥት ቁጥጥር አለመኖሩ፤ በስግብግብ ነጋዴዎች አማካኝነት የፍጆታ ዕቃዎች እጥረትና የዋጋ መናር እንዲከሰት ሆኗል ነው የተባለው።

ነዋሪዎች አክለውም፤ በካማሺ ዞን እና በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ አሁንም የተወሰኑ የጸጥታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ሥፍራች የትራንስፖርት አገልገሎት በጸጥታ ኃይሎች እጀባ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው እና ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መካከል ከሦስት ዓመታት በላይ ውጊያ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

በዚህም ምክንያት የአካባቢው ሕዝብ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ በጸጥታ ችግሮችና እና በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ መሆኑ ተነግሯል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here