ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል፤ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የቆላድባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ደጀን አረጋ የ3 ዓመት ልጅ ሕፃን አማኑኤል ወንድማገኝን ከደብረ ማርቆስ ከተማ 06 ቀበሌ በማገት ወደ ጠገዴ ወረዳ እርጎየ ቀበሌ ጫካ በመውሰድ ቤተሰቦቹ 500 ሺሕ ብር እንዲያመጡ ሲጠይቅ የነበረ ሲሆን፤ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጠገዴ ወረዳ ኮምኒኬሽን ገልጿል።
ሕጻኑን በጫካው ውስጥ ለ7 ቀን ያክል ይዞ ቤተሰቦቹን 500 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ሲጠይቅ ከቆየ በኃላ ፖሊስ ባደረገው ኦፕሬሽን ሕጻኑን ከአጓቾች እጅ ማስለቀቅ መቻሉ ተገልጿል።
ፖሊስ ሕጻኑ ታግቶ የነበረበትን ጫካ በመክበብ እና የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ለጊዜው ዋናው አጋች ቢያመልጥም የጉዳዩ ተባባሪ እንደሆነ የተነገረው ጣማለው አስፋ የተባለ ግለሰብ ሕጻኑን እንደያዘ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ የገለጸ ሲሆን፤ ዋናውን አጋች በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ ግለሰቡን ትናንት ሰኔ 14/2015 በቁጥጥር ማዋል መቻሉንም አስታውቋል።
የሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤትም ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን፤ ተጠርጣሪውን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲባል የአካባቢው ማህበረሰብና መላው የፀጥታ መዋቅር ላደረገው ትበብር ምስጋና ማቅረቡ ተገልጿል።
በዚህና መሰል የወንጀል ተግባራት ላይ በሚሰማሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቀጣይም በተጠናከረ መንገድ ርብርብ እንደሚደረግ አሳውቋል።



