ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል ተብሎ በተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠመው የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ሕግ ትግበራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ በለጠ፤ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በ2013 በንግድ ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ ሲሰራበት እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ብለዋል።
“ይህም የሆነው የሚገጠሙት የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ላይ ማሻሻያ በማስፈለጉ እንዲሁም ለቁጥጥር ክትትል አመቺ ባለመሆኑ ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
የፍጥነት መቆጣጠሪያ ገጠማ ስርዓቱ በትራንስፖርት ባለስልጣን መመሪያ ተዘጋጅቶ እስከ 2014 ድረስ ሲሰራ ቢቆይም አዋጭ ሆኖ ባለመገኘቱ እንዲቋረጥ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
አክለውም፤ በየቀኑ በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከቤት መኪኖች ውጭ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ብቻ በመግጠም ለኹለት ዓመታት አገልግሎቱን ሲሰጥ እንደነበርም አመላክተዋል።
ሥራውን በአዲስ ለማስጀመር አዲስ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው፤ “የሚገጠመው ማሽን በአገሪቱ ላሉ ተሽከርካሪዎች ተስማሚ መሆኑን እያረጋገጥ ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያው ብሉቱዝ፣ ጂፒኤስ፣ ፍላሽ እና ዩኤስፒ ኬብል የሚወስድ በመሆኑ ተቆጣጣሪው አካል የ72 ሰዓታት መረጃዎችን በአንድ ጊዜ ማሳየት እንዲያስችል ታስቦ የተሰራ ማሽን መሆኑም ተመላክቷል።



