ለ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና መዘጋጃ የሚሆኑ ኮርሶች መዘጋጀታቸው ተነግሯል
ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትምህርቱ ዘርፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመሥራት ለተማሪዎች እና ለሠራተኞች በማቅረብ የሚታወቀው ኩራዝ ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግ. ማህበር፤ የትምህርት ሥርዓቱን ማገዝ የሚያስችል አዲስ አገልግሎት ማስጀመሩን በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
የመተግበሪያው ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል የተከናወነ ሲሆን፤ በመድረኩ ላይም አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አዲሱ አገልግሎት “ኩራዝቴክ” የኦንላይን ትምህርት መማሪያ እና ዲጂታል መጽሐፍት ማንበቢያ መተግበሪያ ሲሆን፤ በዚህ መተግበሪያ ከየትኛውም የዓለም አገር ያሉ ተማሪዎች፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ኮርሶችን የሚወስዱበት እና መጽሐፍት የሚያገኙበት መንገድ መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተነግሯል።
በተጨማሪም ኩራዝ ቴክኖሎጂስ ለ12ተኛ ክፍል የፈተና መዘጋጃ የሚሆኑ 21 በሚሆኑ ከ600 በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በማሰባሰብ፤ የ4 ዓመት የተፈጥሮ ሳይንስ የብሄራዊ ፈተና አሠራርን በቪድዮ በታገዘ መልኩ ማዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
ለተማሪዎቹ የተዘጋጁት ኮርሶች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም ተቋማት የሚሰሩ አስተማሪዎች ጋር በመሆን መዘጋጀታቸውን በኩራዝ ቴክኖሎጂ የመተግበሪያዎች ዲቨሎቨር ወጣት ብስራት ሃይሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በዚህም ተማሪዎች በሚፈልጉበት ሰዓት እንዲማሩ ቪድዮዎች እና ሌሎች የሚያግዙ “ፒዲኤፍ” እና ”ፓወርፖይንት ፋይሎች” አብረው በመተግበሪያው ላይ እንደሚገኙም አስረድቷል።
ለ12ተኛ ክፍል የፈተና መዘጋጃ የተዘጋጁት ኮርሶች ከ2011 ጀምሮ እስከ 2014 ያሉ የማጠቃለያ ፈተናዎችን መሆናቸውን የገለጸው ብስራት፤ ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች ፈተናዎቹን እያብራሩ ለተማሪዎቹ ያለገደብ የሚያስጠኑበት መንገድ መመቻቸቱን ገልጿል፡፡
ተማሪዎቹ አንድ ኮርስ ላይ ያሉበትን ደረጃ ማየት የሚችሉበት በኮርሶቹ መጨረሻ ላይ ተማሪዎች ራሳቸውን ለመፈተን የሚጠቀሙበት ጥያቄዎች፣ በዩኒቨርሲቲ የሚሰጡ ኮርሶች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎች እስከ አሰራራቸው እንዲሁም ስለ ሶፍትዌር ማበልፀግ፣ ግራፊክስ ዲዛይን እና ሌሎችም ትምህርቶችም በመተግበሪያው ውስጥ መካተታቸውም ተነግሯል፡፡
ኮርሶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውም የተነገረ ሲሆን፤ በመተግበሪያው ላይ ኮርሶቹ በዓመተምህረት፣ በኮርስ አይነት እና ኹሉንም በአንድ በሚሉ ጥቅሎች መዘጋጀታቸውን ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ኮርስ በመምረጥ በኦን ላይን የክፍያ ስርዓት (ቴሌብር እና ቻፓ የክፍያ መንገድን) ወይንም በቀጥታ በባንኮች በኩል በመክፈል አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል።
በዚህ መተግበሪያ ያሉት ኮርሶች ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ በሥራ ላይ ላሉ ሰዎችም ተጨማሪ ችሎታዎች እና እውቀት የሚያሻሽሉባቸው እንዲሆኑ ታስበው የተዘጋጁ መሆናቸውን የኩራዝ ቴክናሎጂመስራች አባል ወጣት እርግበ ጌታሁን ገልጻለች።
በዚህም መተግበሪያው ደራሲያን መጽሐፍቶቻቸውን በቀላሉ ለሰዎች ተደራሽ እንዲሆን የሚረዳቸው ሲሆን፤ ደራሲያን ያለ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ፕላትፎርሙ ላይ መሸጥ፣ ለደራሲያን የተዘጋጀውን መተግበሪያ በመጠቀም የመጽሐፍቶቻቸውን ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚችሉ አስረድታለች።
“መጻሕፍት “ዳውንሎድ” ተደርገው ለሌሎች ሰዎች ማጋራት እንዳይቻል ይቆለፋሉ” ያለችው እርግበ፤ አንባቢያን መጻሕፍቱን ስክሪንሾት ወይም ሪከርድ እንዳያደርጉት ተደርጎ መተግበሪያው መሰራቱንም ገልጻች።
መተግበሪያው ከአገር ውስጥ እና ከውጪ የተመረጡ 4 ቋንቋዎችን በመጠቀም አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል የተገለጸም ሲሆን፤ መተግበሪያውን በሦስት መንገዶች ማለትም በዌብ ሳይት፣ በኩራዝቴክ ሞባይል መተግበሪያ እንዲሁም በቴሌ ብር ሱፐር አፕ በኩል ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል።
በተጨማሪም አሁን ላይ የ12ተኛ ክፍል ትምህርቶችን ለደህንነት ሲባል፤ በሞባይል መተግበሪያ ብቻ ለተጠቃሚዎች መቅረቡም ተገልጿል።



