በመቱ ከተማ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ተሰማ

0
649

አርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን መቱ ከተማ ከምሽቱ 11 ሰዓት ተኩል በኋላ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ማንኛውን ተሸከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ መታገዱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እገዳው የተጣለው ከባለፈው ሰኞ ሰኔ 12/2015 ጀምሮ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዞኑ ሥር በሚገኘው አሌ ወረዳ በተመሳሳይ ሁኔታ ተሸከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ ከታደገ ቀናት ማስቆጠሩ ተጠቁሟል።

የእገዳው ምክንያት በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በሰፊው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተከትሎ፤ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እና የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎቹን አድኖ ለመያዝ በሚል መሆኑም ነዋሪዎቹ አመላክተዋል።

በዚህም ሳቢያ ማህበረሰቡ ከቦታ ቦታ ለመስቀሳቀስ በእጅጉ እየተቸገረ ነው የተባለ ሲሆን፤ በተለይም ከመኖሪያቸው ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው የሚሰሩ ሰዎች በሰዓት ሥራ ቦታቸው ለመድረስም ሆነ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

በተለይ በከተማው ሰፊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከእገዳው ጋር ተያይዞ ባለንብረቶች ለችግር መዳረጋቸው ነው የተገለጸው።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በመቱ ከተማ አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ፣ በከተማዋ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በሰፊው የሚሠጠው ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ መሆኑን በመጠቆም፣ “እገዳው ከተጣለ በኋላ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“ባለትዳር እና የልጅ አባት ነኝ” ያሉት አሽከርካሪው፤ “ሌላ ዕለታዊ የገቢ ምንጭ ስለሌኝ ቤተሠቤን ለማስተዳደር ተቸግሬያለሁ።” ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ተከትሎ፤ “ከከተማዋ በመውጣት ወደ ገጠር ቀበሌዎች የትራንፖርት አገልግሎት በምንሰጥበት ወቅትም ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ስጋት ውስጥ ሆነን ነው።” ሲሉ አሽከርካሪዎቹ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here