አርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተጣለው ዕቀባ መንግሥትን እንጂ እርሳቸው የሚመሩት ተቋምን እንደማይመለከት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት ይህን የተናገሩት የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን፤ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኔ 16/2015 ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ባቀረቡት የበጀት ዓመት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት፤ የመንግሥትና የንግድ ተቋማት የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌ ብር እንዲፈፅሙ በማድረግ 30.5 ሚሊየን በላይ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎችን ማፍራት መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም 394.7 ቢሊየን ብር በላይ በቴሌ ብር ግብይት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ከሥራ አስፈፃሚዋ ሪፖርት በኋላም ከቋሚ አባላቱ በኩል የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ‹ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር ምን እየተሰራ ነው›፤ ‹ ገደብ የተጣለበት ኢንተርኔት ተቋሙ ለሚያካሄደው ስራዎች እንቅፋት እየሆነ ነው ይህን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው › የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም በጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት መልሶ ለመገንባት ተቋሙ ጥረት እያደረገ መሆኑ የጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ የተወሰኑ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችንና ስርቆቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡
በኢንተርኔት ላይ የተጣለው ገደብ ተቋሙን የሚመለከት ሳይሆን፤ በመንግሥት አካል የተጣለ ገደብ ስለሆነ ከሚመለከተው አካል በሚሰጥ ፍቃድ የሚነሳ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ገደቡን የጣለው የትኛው የመንግሥት አካል እንደሆነ ግን ከመግለፅ መቆጠባቸውን የአሻም ዘገባ አመላቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከየካቲት ወር መጀመሪያ አንስቶ በኢንተርኔት አገልግሎቶች ማለትም በፌስቡክ፣ ሜሴንጀር፣ ቴሌግራም እና ቲክቶክ ላይ ገደብ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ የቪፒኤን መጠቀሚያ ፍላጎትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ማድረጉ ይታወቃል፡፡



