የኢድ አል አድሃ በዓል ኃይማኖታዊ ይዘት እና አከባበር

0
654

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ በዓል ዋነኛው ነው። አረፋ የሚል ሌላኛ መጠሪያ ያለው ይህ ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል፣ በመላው ዓለም በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

አዲስ ማለዳ የበዓሉን ኃይማኖታዊ ይዘትና አከባበር በተመለከተ ከአብዱልሰመድ ነስሩ (ኡስታዝ) ጋር ቆይታ በማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎችን በማገላበጥ የሚከተለውን ጥንቅር አሰናድታለች።

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ዘንድሮ ለ1444ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉ መሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከሐጅ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው።

ሐጅ ማለት ደግሞ እስልምና ከተገነባባቸው ማዕዘናት አንዱ ነው፡፡ ነብዩ መሀመድ እስልምና በአምስት ነገር ተገንብቷል ካሉ በኋላ መጨረሻ ላይ የጠቀሱት የሐጅ ተግባርን ነው።

የሐጅ ስነ ስርዓት ማንኛውም አቅም ያለው ሙስሊም ወደ ጥንታዊት ከተማ መካ በመሄድ ኃይማኖታዊ ተግባራትን የሚፈጽምበት ስርዓትም ነው።

የበዓሉ ታሪካዊ ዳራ ሲጠቀስም፣ ኢድ አል አድሃ እንዲሁም የሐጅ ስነ ስርዓት ከነብዩ ኢብራሂም ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል። አንዳንድ የእምነቱ ሊቃውንት የኢብራሂም ውርስ ወይም <<Legacy of Ibrahim>> ሲሉ እንደሚጠሩትም ይነገራል።

ወደ ጥንታዊት ከተማ መካ ለሐጅ የሄዱ የሐጅን ስነስርዓት ሲፈጽሙ፣ ሐጅ ያልሄዱ በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን ደግሞ የኢድ አል አድሃን በዓል በቤታቸው ሲያከብሩ የሚያከናውኑት እያንዳንዱ ተግባር ከነብዩ ኢብራሂም ጋር የሚገናኝ ነው።

የበዓሉ ቀን የሚፈጸሙ የእርድ ተግባራትም ይሁኑ ሐጅ የሄዱ ሰዎች አረፋ ተራራ ላይ የሚፈጽሟቸው ሁነቶች በሙሉ ከነበዩ ኢብራሂም እና ከቤተሰቦቻቸው እንደማይወጡ ይነገራል፡፡

ነብዩ ኢብራሂም ሀጄራ ከምትባል አጋራቸው የበኩር ልጃቸውን ኢስማኤልን ከወለዱ በኋላ፣ በቤታቸው እንዲቀመጡ በወቅቱ መካን የነበረችው ባለቤታቸው ሳራ ውስጧ አልፈቀደም ነበርና፣ ሀጄራንና ኢስማኤልን ይዘው ወደ አረቢያ ምድር እንዲወጡ አላህ ነብዩን አዘዛቸው።

በዚህም ነብዩ ኢብራሂም የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ልጃቸውን እና እናቱን በማስከተል የሰው ዘር፣ አዕዋፍት ሳይቀር ምንም ወዳልነበረባት ወደዚያን ጊዜዋ ምድረ በዳ፣ የአሁኗ መካ መሄዳቸው ይተረካል።

ሆኖም ግን ነብዩ ኢብራሂም ትንሽዬ ቴምር እና ውሃ አስቀምጠው ጡት ያልተው ልጃቸውንና እናቱን ትተው ሲመለሱ፣ ሀጄራ ወዴት ትሄዳለህ ስትል ትጠይቃቸዋለች። ከነብዩ ምላሽ አላገኝ ያለችው ሀጄራም አላህ ነው ወይ ያዘዘህ ስትል አጥብቃ ስትጠይቃቸው፣ አንገታቸውን በማወዛወዝ አዎ ሲሉ መለሱላት።

ይህን የተገነዘበችው ሀጄራም ወደ ልጇ ተመልሳ ፍጥረት በሌለበት ምድረበዳ ከአንዱ ተራራ ወደ ሌላኛው ተራራ እየተመላለሰች የሚጠጣ ውሃ ለእሷና ለልጇ ብታስስም በቀላሉ ልታገኝ አልቻለችም ነበር።

በዚህም ዛሬ ላይ ወደ መካ ለሐጅ ስነስርዓት የሚሄዱ የእምነቱ ተከታዮች ከሚፈጽሟቸው አብይት ተግባራት መካከል የሀጄራን ገድል ለማስታወስ በተራሮች መካከል መመላለስ መሆኑ ይጠቀሳል።

ሀጄራ ውሃ ፍለጋ ትመላለስበት በነበረው ተራራ ላይ አንድ ተዓምር ይፈጠራል። ይህም የሰማይ መላዕክ በክንፉ መሬቱን በመብሳት ውሃ ማፍለቁ ነበር። ይህ ውሃ የሀጄራን እና የልጇን ህይወት ከመታደግ ባለፈ፣ ሌሌች ይህን የሰሙ ሰዎችም በውሃ ጉድጓዱ ዙሪያ ጎጆ እንዲቀልሱ በማድረግ የዛሬዋ መካ ከተማ እንድትቆረቆር ምክንያት መሆኑ ነው የሚነሳው።

ዛሬም በዓሉን ለማክበር ወደ መካ ለሐጅ የሚሄዱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ይህን በማስታወስ ከውሃው ይዘው ይመለሳሉ። እንዲሁም ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው ኢስማኤል የሰባት ዓመት ህጻን ሳለ በተደጋጋሚ ያዩት ህልም ከኢድ አል አድሃ በዓል ጋር በቀጥታ ይያያዛል።

ነብዩ በህልማቸው ኢስማኤልን ሲያርዱት አይተው ነበርና ይህ ከፈጣሪ የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል <<እኔ በህልሜ አንተን የማርድህ ሆኘ አይቻለሁ>> በማለት ለኢስማኤል ሲነግሩት፣ ልጃቸውም <<ይህ የአላህ ትዕዛዝ ነው፣ የታዘዝከውን ፈጽም>> ይላቸዋል።

ነብዩም ልጃቸውን ለማረድ ወደ ተራራ ይዘውት እየወጡ ሳለ፣ ሰይጣን በአባት ወይም በልጅ ልቦና ሰርጎ በመግባት የፈጣሪን ትዕዛዝ ለማሰናከል ብዙ ቢጥርም፣ ነብዩ ኢብራሂም ሰይጣንን በጠጠር እየወገሩ ልጃቸውን ሊያርዱ ሲዘጋጁ ከሰማይ በግ ተሰጣቸው። በኢስማኤል ምትክም ታረደ።

የበዓሉ ዕለት ከኢድ ስግደት በኋላ፣ የሚታረደው በግ ለመብል ብቻ ሳይሆን ትልቅ ኃይማኖት ዕሴት እንዳለው ነው የሚገለጸው። የሚፈጸመው የእርድ ተግባርም ነብዩ ኢብራሂም እና ልጃቸው ኢስማኤል ለፈጣሪያቸው የነበራቸውን ፍጹም ታዛዥነት ለማስታወስ መሆኑን የእምነቱ አስተማሪዎች ያወሳሉ።

የኢድ አል አድሃ በዓል በሚከበርበት ዕለት ህዝበ ሙስሊሙ ወደ ሜዳ በመውጣት የኢድ ሰላት ያከናውናል። ከዚህ መልስም ነው የእርድ ተግባር የሚፈጸመው። በዕለቱ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸምው የእርድ ተግባርም ከግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል ውጭ እንዳይሆን ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ መኖሩም ነው የሚጠቀሰው።

እርዱ ከተፈጸመ በኋላም አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ለቤተሰብ፣ አንድ ሶስተኛው ለጎረቤትና ለዘመድ እንዲሁም አንድ ሶስተኛው ለድሆች የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህ ዕለት ስጋ እጥተው ተርበው የሚውል እንዳይኖሩ በሚል ነው።

ከግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል ውጭ ሌላ የእርድ እንስሳት የማይፈጸምበት የተጻፈ ምክንያት ባይኖርም፣ ለምሳሌ የበዓሉ ዕለት ዶሮ ማረድ የማይቻለው ስጋዋን ለማከፋፍል ስለማይበቃ እንደሆነ ይነሳል።

በዕለቱ ለበዓሉ ተብሎ የሚታረዱ እንስሳት ከሚገዘቡት ወቅት ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግም የማይዘነጋ ነው። ይህ ለአላህ የሚቀርብ ነገር ነውና ያማረና ንጹህ መሆን ስላለበት፣ አንዱም ይሁን ኹለቱ ዓይኑ የጠፋ፣ ጆሮው የደነቆረ፣ ሽቫ የሆነ በጥቅሉ አንዳች የጤና እክል ያለበት እንስሳት ለእርድ አይበቃም።

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በኹሉም የአገሪቱ ክፍል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት፣ ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ባህላዊ እሴቶች ጭምር ተካተውበት በድምቀት እንደሚከበር ይጠቀሳል።

ለበዓሉ የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራቶች ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ እናቶች ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቤት እንዳፈራው ያዘጋጃሉ።

ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳት እና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ሥራ ተጠምደው ይታያሉ፡፡ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ቢሆኑ ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻዎች አሏቸው፡፡

ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ የአባቶችና የወንድ ልጆቻቸው ድርሻ ነው።

እንዲሁም የበዓሉ ማህበራዊ ፋይዳ የላቀ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ በተለይ በከተማ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች በገጠር የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ የሚጠቀሙበት መልካም እድል መሆኑም ይነሳል።

ስለዚህም በሥራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውን የሙስሊም ቤተሰብ ከያለበት አሰባስቦ ለማገናኘት የአረፋ በዓል ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡

በተጨማሪም የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ ወጣቶች የሚሞሸሩበት፣ ሌሎችም የወደፊት ትዳራቸውን ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበት እና በባህሉ መሰረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የእምነቱ ተከታይ አባቶች ሳይጠቅሱ አያልፉም።

እንዲሁም በተጣሉ ሰዎች መካከልል እርቀና ሰላም እንዲወርድ በማስቻል ረገድም የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው በእምነቱ አስተምህሮ የሚገለጸው።

ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጆች፣ ጎረቤታሞች እንዲሁም በማህበረሰብ መካከል የተፈጠሩ ያለመግባባቶች ካሉ በአረፋ በዓል ሰሞን ይቅር በመባባል ሰላምን እና እርቅ ያወርዳሉ።
ለበዓሉ የተዘጋጁ የምግብ እና የመጠጥ ዓይነቶችን አብሮ በመብላትና በመጠጣት፣ የቤተሰብ ህይወት እንዲሻሻል እንዲሁም የአገር ሰላም እንዲሰፍን ምክክሮች ይደረጋሉ።

በዚህም በበዓሉ ሰሞን ከመብላት እና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች በርከት ያሉ ቤተሰባዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ይከናወናሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ በጉራጌ ስልጤ እና ወለኔ ማህበረሰብ ዘንድ በተለዬ ድምቀት እንደሚከበር የተገለጸ ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢዎች በዋዜማ የጎመን ክትፎ ስርዓት መኖሩም ይነሳል።

በተለይም በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው ትልቅ በዓል አረፋ መሆኑ ይነገራል።

በዓሉ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ዝግጅት የሚጀምር ሲሆን፣ ሴቶች ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቆጮ በማዘጋጄት አባወራዎች ደግሞ ለእርድ የሚሆን ሠንጋና የማገዶ እንጨት በማቅረብ በዝግጅቱ ይሳታፋሉ።

ልጃገረዶች በተጨማሪም ግቢ በማጽዳት እና በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት ቤቶችን በማስዋብ ያግዛሉ።

በበዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደየአካባቢያቸው የሚገቡብትም ነው።

በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ በአረፋ በዓል ወደ ቤተሰቡ ያልመጣ በሕይወት እንደሌለ ይቆጠራል፣ ቤተሰብንም ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡

ደግሞ በዋናነት በበዓሉ ሰሞን የሚጀመረው የልጃገረዶች ጭፈራ የአረፋ በዓልን በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው ሲሆን፣ ልጃገረዶች ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚጨፍሩበት ወንድ ወጣቶችም አብረው በመጫዎት ለወደፊት የምትሆን የትዳር አጋራቸውን የሚያጩበት ደማቅ በዓል ነው፡፡

ይህም የአረፋ በዓልን የመተጫጫ እና የጋብቻ ወቅት ነው ያስብለዋል፡፡

በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ በበዓሉ ዋዜማ የሚከበረው የሴቶች አረፋ ሆኖ የወንዶች ደግሞ የበዓሉ ስግደት በሚከናወንበት ዕለት ይከበራል።

በሴቶች አረፋ ክልፋን (የተከተፈ ጐመን) አተካና (ቡላ፣ አይብና ቅቤ) የተለመዱ ባህላዊ ምግቦች መሆናቸውም ይጠቀሳል።

በበዓሉ ዕለት በሽማግሌዎች ከተመረቀ በኋላም የእርድ ተግባሩ ይቀጥላል። የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ክፍል በድምቀት የሚከበር ይሁን እንጂ፣ በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ ግን በተለዬ ድምቀት የሚከበር መሆኑ ነው የሚነሳው።

የአረፋን በዓል ከሌሎች የእስልምና እምነት በዓላት የሚለየው ዘለግ ያለ መሆኑ ነውም ይባልለታል።
ከዋዜማው ጀምሮ መከበር የሚጀምረው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል፣ ከዕሮብ ቀጥሎ ባሉት ሀሙስ፣ አርብ እና ቅዳሜ ሶስት ቀናትም ደምቆ እንደሚሰነብት ነው የተጠቆመው።

ኢትዮጵያ የቀደምት የእስልምና እምነት ተቀባይ አገሮች ስም እንዲሁም የእስልምና ታሪክ ሲነሳ ስሟም አብሮ ይነሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here