ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 3/2012

0
800

1 በኢትዮጵያ ከ 1900 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የቴክኖ ሞባይል አምራች ድርጅት አስታወቀ።ድርጅቱ በትኩረት ከሚሠራባቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ባሻገር በአገሪቱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በኢትዮጵያ የቴክኖ ሞባይል ድርጅት የገበያ ልማት ሥራ አስኪያጅ ሐሳኒ ሞሀመድ ገልጸዋል።በአሁኑ ወቅት በጎሮ አይሲቲ ፓርክ ግዙፍ ፋብሪካ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ ቀደም ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችለዋልም ብለዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………

2-የጀርመን ልማት ባንክ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ 29 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ።ድጋፉ በዘርፉ የሚታየውን የትብብር ስልጠና ለማጠናከር ያለመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የርክክብ ስነ-ስርዓቱም በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ተካሂዷል።በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነርን እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የጀርመን ልማት ባንክ ተወካዮች፣ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

…………………………………………………………………………………

3-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሼባ ማይልስ ቋሚ ደንበኞች ፕሮግራም የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት እና የአየር መንገዱን የደንበኞች ቀን ህዳር 2/2012 አክብሯል።በዓሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው(ዶ/ር)፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት  ተከብሯል።የአየር መንገዱ ደንበኞች የሼባ ማይልስ አባልነት የተለያዩ ደረጃዎች ሲኖሩት በየደረጃዎቹ መሰረትም የተለያዩ ተጨማሪ አገልገሎቶችን እንደሚያገኙና አሁን ላይ ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ቋሚ አባላት እንዳሉት አየር መንገዱ አስታውቋል።(አዲስ ማለዳ)

…………………………………………………………………………………

4-የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና መስጠት መጀመሩን የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር  አሸናፊ አምብሬ  ገልጸዋል።የሆስፒታሉ የፕላስቲክና ቀዶ ሕክመና ክፍሉ ሕክምናውን የሚሰጡ የባለሙያዎች ቡድንና የሕክምና ግብዓቶን አሟልቶ ለታካሚዎች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል።የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከሚሰጥባቸዉ ዉስጥ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸው፣ በእሳት አደጋ ቃጠሎ የደረሰባቸውና በአካሎቻቸው ላይ የጠባሳ ማስተካከል እንደሆኑም ተናግረዋል።በተጨማሪም የጭንቅላት ቀዶ ህክምና፣ በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱትን የነርቭ ዘንግ ክፍተት ህክምና እንዲሁም፤ የተመረዙ ሰዎች የሚታከሙበት የቶክሲኮሎጂ ማዕከልና የልብ ህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም  አሸናፊ ገልጸዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 )

…………………………………………………………………………………

5-በአዲስ ከተማ አስተዳደር ከ5 ሺሕ በላይ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ወደ ስራ ሊያሰማራ መሆኑን የከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ  ነስረዲን ሙሐመድ አስውቀዋል።በባለፉት ቀናት በከተማዋ በሚገኙ የተለዩ ክፍለ ከተሞች ከ20 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመራቸውን ገልጸው እነዚህ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የገጽታ ግንባታ ከመቀየር ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አቶ ነስረዲን ተናግረዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

…………………………………………………………………………………

6-በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ ፓርኩን ከጎበኙ ከሰባት ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ሰባት ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር የአካባቢው ማኅበረሰብና መንግስት ገቢ ማግኘታቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቋ።የሰሜን ተራራች ብሄራዊ ፓርክን የሚጎበኙ የውጪ አገር ቱሪስቶች ቁጥር ካለፉት ዓመታት በተሻለ እየጨመረ መምጣቱን  የጽህፈት ቤቱ የሕብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ  ታደሰ ይግዛው ገልጸዋል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ አለመረጋጋት ቢከሰትም ፓርኩን የሚጎበኙ የውጪ አገር ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።(ዋልታ)

…………………………………………………………………………………

7-የኢትዮጲያ ኤልክትሪክ ሃይል አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 38 ሚለዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደተሰረቀ አስታውቋል።የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘራፊዎች በትራንስፍርመሮች ላይ እያካሄዱት ባለው ስርቆት ምክንያት ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።በየጊዜው ከደንበኞች የሚደርሰውን ቅሬታ ለመፍታት እየሰራን ቢሆንም ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የትራንስፎርመራና የኬብሎች ስርቆት መበራከቱን ተናግረዋል።አንዱ ትራንስፎርመር ከ 200 እስከ 300 ለሚሆኑ ደንበኞች ማገልገል የሚችል  ሲሆን የ አንዱ ትራንስፎርመር ዋጋ ከ400 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ወጪ ተደርጎበት ከውጭ አገር የሚገባ እንደሆን አቶ መላኩ ገልጸዋል ።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 )

…………………………………………………………………………………

8-ኢቦላን ለመዋጋት የመጀመሪያ እርምጃ ነው የተባለለት የመጀመሪያውን የኢቦላ በሽታ መከላከያ ክትባት በአለም የጤና ድርጅት (WHO)  ተቀባይነት ማግኘቱን ተነግሯል።ኢቨርቦ የሚል ስያሜ የተሰጠው የክትባት መድሃኒቱ በመርኪ ፋርማቲካል ኢንዱስትሪ የተመረተ ሲሆን   በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሙከራ ሲደረግበት መቆየቱን ጠቅሷል።ክትባቱ በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ተቀባይነት ከማግኘቱ ጋር በተያያዘ አለም የኢቦላ መከላከያ መድሃኒት አግኝታለች ማለት እንደሚቻል ተገልጿል።ክትባቱ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ገበያ ላይ እንደሚውል ታውቋል።(ኢዜአ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here