ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በመድኃኒት እና በደም እጥረት የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ሽታዬ በቀለ፤ በዞኑ አስራ ሰባት ወረዳዎች ሥር በሚገኙ የጤና ተቋማት ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን በመጥቀስ፣ ይህም የሕክምና አገልግሎትን ለሕብረሰተቡ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ካለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞም የወደሙ እና የተቃጠሉ የጤና ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ከፍተኛ የደም እጥረት በመኖሩና ከደም ጋር የተያያዙ የሕክምና አግልግሎቶች በሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡ በመሆናቸው ወላድ እናቶች ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።
ይህም ከወቅታዊ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ነቀምት ከተማ ከሚገኘው የደም ባንክ ቅርንጫፍ ሄዶ ለሆስፒታሎች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ የተነሳ የተፈጠረ ችግር ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ለዚህ ጉዳይ እልባት ለመስጠትም ከክልል ጤና ቢሮ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት አድርገናል ያሉት ኃላፊዋ፤ እስካሁን የተሰጠ መፍትሄ አለመኖሩን አመላክተዋል፡፡
የጊዳ አያና አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሂርኮ ምትኩ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ከመድሐኒት እና በተለይም ለወላድ እናቶች ከሚለገስ ደም እጥረት ጋር ተያይዞ የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ “አሁን ባለንበት ሰኔ ወር ብቻ በወሊድ ጊዜ ከደም እጥረት ጋር ተያይዞ የሦስት እናቶች ህይወት አልፏል።” ሲሉ አውስተዋል፡፡
ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞም ከፍተኛ ችግር መኖሩን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ታካሚዎች ከግል መድኃኒት መደብሮች በተጋነነ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውንም አብራርተዋል፡፡
ሆስፒታሉ በአሁን ሰዓት እንደ ጊዳ አያና፣ ኪረሙ፣ ኤበንቱ፣ ሊሙ እንዲሁም ሀሮ ሊሙን ከመሳሰሉ አጎራባች ወረዳዎች ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
“ይህም የሆነው በነዚህ ወረዳዎች ያሉ አብዛኞቹ የጤና ጣቢያዎች ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ነው።” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በዚህም ምክንያት በቀን እስከ 200 ታካሚዎች ይቀበል የነበረው ሆስፒታሉ፤ አሁን ከአቅም በላይ 600 የሚሆኑ ታካሚዎችን እንደሚቀበል አስረድተዋል፡፡



