የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎት መረጃ ለማግኝት የሚያስችል የጥሪ ማዕከል ይፋ ተደረገ

0
565

ከሀምሌ 1 ጀምሮ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን መሰጠት እደሚጀመር ተገልጿል

ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አገልግሎት መረጃ ለማግኝት የሚያስችል 965 የተባለ የጥሪ ማዕከል ይፋ አድርጓል፡፡

በሚኒስቴሩ የጥራት መሠረተ ልማትና ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፤ የጥሪ ማዕከሉ መከፈት የንግድ ሥራን ለመጀመር የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ተቋማት በኹሉም የአገልግሎት አይነቶች ላይ ሙሉ መረጃ ለማግኘት እንዲችሉ የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የንግድ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከሀምሌ 1 /2015 ጀምሮ በኹሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት በኦን ላይን መሰጠት እደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡

የንግድ ሥራን የመጀመር ሂደትን አመቺ ለማድረግ፣ ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት እና የንግድ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከኹሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሀላፊዎች በድርጅት ሥም፣ በንግድ ሥም፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ እና በአጠቃላይ በ19 አገልግሎቶች ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here