በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ታጣቂዎች በመንግሥት በጀትና ተሽከሪካሪ ተመድቦላቸው እንደሚንቀሳቀሱ ተገለጸ

0
589

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በመንግሥት በጀትና ተሽከርካሪ ተመድቦላቸው እንደሚንቀሳቀሱ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ ተሰማ ከአዲስ ማለዳ ማለዳ ጋር ባደርጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።

ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በሰላም ለመኖር ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም በካማሽና መተከል ዞኖች በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ከነትጥቃቸው ካምፕ ገብተው በመንግሥት የሚቀለቡ መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ሌሎች ደግሞ በመንግሥት በጀትና ተሽከርካሪ ተመድቦላቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

በክልሉ ከሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ሳይቀር ድጋፍ እንዳላቸው በማንሳትም፣ የፋኖና የሸኔ ታጣቂዎች ትጥቅ ሳይፈቱ እናንተም እንዳትፈቱ በማለት ታጣቂዎችን የሚሰብኩ የመንግሥት አመራሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም ፓርቲያችን በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ወደ ወንበራ ወረዳ በሄደበት ወቅት፣ የዞኑ አመራር ጉባኤያችንን ለማስተጓጎል እነዚህን ታጣቂዎች ተሽከርካሪ መድቦ ልኳል ነው ያሉት።

ታጣቂዎቹ ከሱዳን እና ከጫካ የገቡት ሰላማዊ ህይወትን ለመምራት ተስማምተው እስከሆነ ድረስ መለማምጥ አያስፈልግም ካሉ በኋላም፣  መንግሥት ከሽፍታ ጋር የሚያደርገውን አላስፈላጊ መለማመጥ በመተው ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈልገ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ውጭ የሚንቀሳቀስ ኃይል ሊኖር እንደማይገባ ጠቅሰው፣ ይህ ካልሆነ ግን ሌላው የማህበረሰብ ክፍልም ራሱን ከጥቃት ለመከላከል ሲል መታጠቁ አይቀሬ ነው ብለዋል።

በክልሉ በስፋት ይንቀሳቀሳሉ የተባሉት የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) እና የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎች ሲሆኑ፣ በዚህ ወቅት ብሬን፣ ዲሽቃ፣ ስናይፐርና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ታጥቀው እንደሚንቀሳቀሱ ተመላክቷል።

ይህን ተከትሎም በክልሉ ከቦታ ቦታ በነጻነት መንቀሳቀሰ እዳጋች መሆኑም ነው የተጠቀሰው። ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በሚፈጽሙት ጥቃት በሰዎች ህይዎትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ስማቸው ይነሳል።

ዮሐንስ ተሰማ ከአዲስ ማለዳ ጋር ያደርጉትን ሙሉ ቃለ መጠይቅ በዚሁ ቻናል ላይ የምታገኙት መሆኑን እንገልጻለን።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here