በሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኘው ኮዬ ፈጨ ኮንዶሚኒየም ለባለእደለኞች በተላለፉ ቤቶች ውስጥ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ቁልፍ ሰብረው በመግባት ወረራ እየፈጸሙ መሆኑን የኮንዶሚኒየሙ ህጋዊ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በኮንዶሚኒየሙ የእጣ እድለኞች ሆነው ለባለቤቶቹ ቁልፍ ተላለፎ ነገር ግን ተቆልፈው በተቀመጡ ቤቶችና እስካሁን ለባለእድለኞች ባልተላለፉ ቤቶች ላይ የማይታወቁ ሰዎች ሰዎች ወረራ እየፈጸሙ ነው ተብሏል።
ይህን ድርጊት ለመከላከል ጥረት በሚያደርጉ የኮንዶሚኒየም የጥበቃ ሠራተኞች ላይም ዛቻ እና ማስፈራሪያ በማድረስ በኃይል እንደሚገቡ ነው የተገለጸው።
ነዋሪዎቹ አክለውም ‹‹ተዘግቶ የተቀመጠን ቤት በኃይል ሰብረው ገብተው ወረራ ሲፈጽሙ አንድም የመንግሥት አካል ሊያሰቆማቸው የሞከረ የለም›› ሲሉ ተደምጠዋል።
ከመጋቢት 2015 ጀመሮ በኮንዶሚኒየሞቹ ላይ ከፍተኛ ወረራ እየተካሄደ መሆኑን በመጠቆምም፣ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናቀርብም መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም ብለዋል፡፡
በዚህም ወደ ኮንዶሚኒየሞቹ የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን ማንነት ማወቅ ባለመቻሉ ህጋዊ ነዋሪዎችን ስጋት ውስጥ ከቷል ነው የተባለው።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኮንዶሚኒየሙ የጥበቃ ሠራተኛ በበኩላቸው፣ ማንነታቸውን መናገር የማይፈለጉ ሰዎች የተዘጉ ቤቶችን ቁልፍ በኃይል ሰብረው በመግባት እየኖሩበት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አክለውም ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን በመጠቆም፣ ድርጊቱን ማሰቆም አለመቻሉን ገልጸዋል።
ኮንዶሚንየሙን እንድንጠብቅ የተቀጠርነው የጥበቃ ሠራተኞች ደመወዛችን ከተቋረጠ ኹለት ወር በማለፉና ይህን ተከትሎም የጥበቃ ሥራችንን በአግባቡ እየሰራን ባለመሆኑ ህገወጥ ድርጊቱ ተባብሶ ቀጥሏልም ነው ያሉት።
ኮንዶሚኒየሙ የተሰራው ለልማት ተነሽ ለሆኑ በቀበሌ ቤት ለሚኖሩ ሰዎች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ቤቶቹ የመንገድ እና የመብራት መሰረተ ልማት እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቁ መሆናቸውን ተከትሎ ባለእድለኞች ቤታቸውን ቆለፈው እንዳስቀመጡት ተጠቅሷል።
የቤቶቹ መሰረተ ልማቶች እስኪሟሉ ድረስ በሚል ተዘግተው ከተቀመጡት ሌላ ለባለእድለኞች ያልተላለፉ በርካታ ቤቶች መኖራቸው ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ወረራ እንዲፈጽሙ አመች ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው።
አዲስ ማለዳ በጉዳይ ላይ ምላሽ ለማግኘት ለሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡



