በፌዴራል መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራቂት ብሎ በሚጠራውና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መካከል የተጀመረው የሠላም ድርድር እንዲቀጥል የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡
አባላቱ ይህን የጠየቁት ጨፌው አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባደረገበት የኹለተኛ ቀን ውሎ ላይ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ውስጥ በኹለቱ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው የረዥም ጊዜ ውጊያ እልባት እንዲያገኝ እና ሕዝቡም ሰላም አግኝቶ ወደ መደበኛ የዕለት ከዕለት ኑሮው እንዲመለስ የጨፌው አባላት ጥያቄ ማቅረባቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
“በክልሉ ሰላም ከጠፋ ቆይቷል፣ ሕዝቡም ወጥቶ መግባት አልቻለም፣ እዚህም እዚያም ጉልበተኞች በመደራጀት ንጹሃንን እየዘረፉ እና እያሰቃዩ ነው” ያሉት የምክር ቤቱ አባላቱ፤ “በተለያዩ ወረዳዎች ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የመንግሥት መዋቅሮች እየተዘጉ ነው። ይህ ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው መቼ ነው? መጨረሻውስ ምን ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲስ ከአባላቱ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የሰላም ድርደሩ አለመቋረጡን ገልጸው፤ በተደራዳሪዎቹ መካከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች በርካታ በመሆናቸው ምክንያት ለኹለተኛ ዙር መራዘሙን ጠቁመዋል።
“በታንዛኒያ ራስ ገዝ በሆነቸው ዛንዚባር ደሴት የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ድርድር የራሱ የሆነ ጠንካራም ደካማም ጎን አለው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ሆኖ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ የመጨረስ ዝንባሌ በኹለቱም ወገን አለ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፤ “በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እና በመነጋገር ብቻ መፈታት እንዳለበት መንግሥት በጽኑ ያምናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራውና በመንግሥት በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ ነጥቦች፤ የተኩስ አቁም ማድረግ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፖለቲካ እስረኞች መፍታት፣ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጠና ገለልተኛ አካል ማቋቋም እንዲሁም ኹሉን አካታች አገራዊ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ አስተዳደር እየፈረሱ ስላሉ የእምነት ተቋማት እና የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቷል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ የሚመሩት መንግሥት በሕገወጥነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያደርግ ተናግረው፣ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ፕሬዘዳንት ሽመልስ አክለውም “በዚህ ሕገወጥ ግንባታን የማፍረስ ሥራ ላይ ርህራሄ የምታሳዩ የመንግሥት የሥራ አመራሮችም ከድርጊታቹ እንድትቆጠቡ አሳስባችኋለው፣ ካልሆነ ግን እናንተም አብራችሁ ትፈርሳላችሁ።” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡



