በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ባለው የሰላም እጦት ምክንያት ዜጎች እየተገደሉ መሆኑ ተጠቆመ

0
575

መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ከኦነግ ሽኔ ጋር እንዲሁም በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎቸ ጋር በሚያደርገው ውጊያ፤ ዜጎች ለሞትና አስቸጋሪ ሕይወት ለመግፋት መገደዳቸውን አምስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መኢአድ፤ ኢህአፓ፣ እናት ፓርቲ፤ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በአማራ ክልል ኢ-መደበኛ ኃይል ብሎ መንግሥት ስያሜ በሰጠው ፋኖ ላይ በከፈተዉ ጥቃት የአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ የግጭት አዉድማ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት በየቦታዉ ኢ-መደበኛ ኃይሎችን ዒላማ በማድረግ በሚከፍተው ተኩስ ከሰላማዊ የክልሉ ኗሪዎች ጋር የማያቋርጥ ግጭት ዉስጥ በመግባቱ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡

በክልሉ በሚደረጉ የደፈጣ ጥቃቶች በየቦታው የመንግሥት ሹማምንትና ባለሥልጣናትን መግደል የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል ሲሉ አክለዋል፡፡

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በታጣቂ ኃይሎች እጅ በሚገኙ አካባቢዎች ለአራት ዓመታት ለዘለቀ ጊዜ የሰቆቃ ኑሮ እየገፋ እንደሚገኙና በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በማንነታቸዉ ምክንያት ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ነባራዊ እዉነታ መገዳደል ሆኖ ሳለ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የኹለቱም ክልሎች መንግሥታት በማያቋርጥ ስብሰባ ከመጠመድ ያለፈ ምንም ነገር መፈየድ አልቻሉም ሲሉ ፓርቲዎቹ ከሰዋል፡፡ 

መንግሥት ወቅታዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ አምኖ አለመቀበሉን የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፣ ኢትዮጵያን ካንዣበበባት ሁለንተናዊ የጥፋት አደጋ ለመታደግ የሚደረግ ሙከራ አለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡

አገር ቁልቁል እየተንደረደረችና ወደ ጥፋት እያመራች ባለችበት በአሁኑ ወቅት “ኢትዮጵያ ከፍታ ላይ ነች፤ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ነዉ፤ ከብልጽግና መንገዳችን ማንም ወደ ኋላ አይመልሰንም” የሚሉ ዲሰኩሮች አገርን ከመታደግ ይልቅ የጥፋት ጉዞን እያፋጠኑ ነው ብለዋል፡፡

ለወቅታዊ ችግሮች ብቸኛ መፍትሔዉ ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት፤ ነፍጥ አንስተዉ ዉጊያ ላይ በሚገኙ ኃይሎች እና ሕጋዊ እውቅና ኖሯቸው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በኢትዮጵያዉያን በባለቤትነት የሚመራ ወዳጅ አገራት በደጋፊነት የሚሳተፉበት አስቸኳይ የአገር አድን ውይይት ማድረግ ይገባል ሲሉ ፓርቲዎቹ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here