በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ ጯሂት ከተማ ሠመረቻ በተባለ አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ትናንት ሐምሌ 19/2015 ከአምስት ሰአት ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበር የምዕራብ ደንቢያ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አንዱ በሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክትን ለመጎብኘት የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 19/2015 ወደ አካባቢው መጓዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ለአመራሮቹ በሬ መታደረዱን ተከትሎ “በዕሮብ ቀን ለምን በሬ ይታረዳል፤ ኃይማኖታችንስ ለምን ይረክሳል?” በሚል በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩ ተጠቁሟል።
በዚህ የተነሳም በአካባቢው በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት አልፏል ነው የተባለው።
የተኩስ ልውውጡ እየተካሄደ ያለው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ መሆኑን የገለጸው የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት፤ ከጎረጎራ በቅርብ እርቀት በሚገኘውና ሠመረቻ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እስከ ጯሂት ከተማ ደረስ የተኩስ ልውውጡ ተሰፋፍቶ እንደነበር ጠቁሟል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጽህፈት ቤቱ ሠራተኛ “ረፋድ አራት ሰዓት አካካባቢ በጯሂት ከተማ አድርጎ ወደ ጎርጎራ የባለሥልጣን መኪኖች ሄደዋል። የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖራቸውንም ሰምተናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እስከ ትናንት ማታ 12 ሰዓት ድረስ በአካባቢው የተኩስ ልውውጡ መካሄዱን በመጠቆምም፤ በተኩሱ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ወደ ጯሂት ከተማ እየገባ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተኩሱ ልውውጡ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ከፋኖ ታጣቂዎች እና የነዋሪዎች ህይወት መጥፋቱን የጠቆመው ጽህፈት ቤቱ፤ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውንም አክሏል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት አባላት “ቤታችን ድረስ ገብተው ደብድበውናል” በሚል የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደነበርም ተመላክቷል።
በአማራ ክልል የፌደራል መንግሥትና የክልሉ አስተዳደር የህግ ማስከበር ዘመቻ እያደረጉ መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ተባብሰው ቀጥለዋል።



