በትግራይ ክልል ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር በ196 በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

0
376

ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል እየተባባሰ በመጣው ረሃብ ምክንያት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሆስፒታል የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር በ196 በመቶ መጨመሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅሶ ትናንት ሐምሌ 21/2015 ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

በክልሉ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግር፣ ረሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድኃኒት እጥረት ምክንያት በዋናነት አጥቢ እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳት መቻሉን ጠቁሟል።

እንዲሁም በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ መቆሙን ተከትሎ እየተከሰተ ባለ ረሀብ እና የመድኃኒት እጥረት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ነው የተገለጸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ሐምሌ 18/2015 ባወጣው መረጃ መሰረት፤ በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ገልጿል።

የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ሐምሌ 14/2015 ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በክልሉ ተከስቶ የነበረው የሰላም እጦት በክልሉ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ኑሯችውን የምግብ እርዳታ ላይ የተደገፈ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ በጤናውም ረገድ በክልሉ ኮሌራና መሰል በሽታዎች መከሰታቸውን ጠቁሟል።

በትግራይ ክልል በዋናነት ሰብዓዊ ድጋፍ ያቀርቡ የነበሩት የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በእርዳታ ቁሳቁስ ላይ ስርቆት ተፈጽሟል በሚል እርዳታቸውን ያቋረጡ ሲሆን፤ በእዚህም ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድሀኒት እጥረት ማጋጠሙ ተጠቅሷል።

በትግራይ ክልል ያለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያሳስበኛል ያለው ኢሰመጉ፣ በክልሉ ለተከሰተው ረሀብ፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድኃኒት እጥረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ይህ ሰብዓዊ ቀውስ ከዚህ የከፋ ጉዳትን ሳያደርስ ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ የነበሩ የሕክምና ተቋማት በግጭቱ ምክንያት ከደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም እየሞከሩ ቢሆንም፤ ተቋማቱ አሁን ድረስ ያለባቸው የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት፣ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረትና የሕክምና አቅርቦት እና ፍላጎት ተመጣጣኝ አለመሆን ከፍተኛ ችግር መሆኑ ተመላክቷል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለኹለት ዓመታት የቆየው ጦርነት ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢቆምም፤ ግጭቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም ተብሏል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here