በየዓመቱ መድኀኒት በተላመዱ በሽታዎች ምክንያት የ35 ሺሕ ሰዎች ሕይወት ያልፋል

0
874

በኢትዮጵያ የፀረ ተዋህስያን መድኀኒቶች በጀርሞች መለመድ ወይንም አልበገር ባይነት ምክንያት በየሰዓቱ የአራት ሰዎች ሕይወት እንደሚያልፍ ይፋ ሆነ።
ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ 35 ሺሕ በላይ ሰዎች በዓመት ለሞት እንደሚዳረጉ ተገልጿል።

የፀረ ተዋህስያን መድኀኒቶች ጀርሞችን መልመድ ወይንም አልበገር ባይነት ምክንያት በዓለም እስከ 750 ሺሕ ሰዎች እየሞቱ እንደሚገኙ እና በቀጣይ ዐስር ዓመታትም አሁን ባለበት ደረጃ ከቀጠለ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ ዐስር ሚሊዮን ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቋል።
ከችግሩ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ በአንድ ሰዓት ውስጥ 86 ሰዎች እንደሚሞቱ የሚያሳየው መረጃው ከተዋህስያን ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፉባት አፍሪካ በሰዓት 36 ሰዎች እንደሚሞቱ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም በቀላሉ ይታከሙ የነበሩ በሽታዎችን ለማከም እና ለማዳን ከፍተኛ ችግር እየገጠመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ሰዎችን ለተጨማሪ ወጪ በመዳረግ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍጠር ላይ ነው ተብሏል።

እነዚህ በሰዎች እና በእንስሳት በባክቴሪያኅ በቫይረስ፣ በፈንገስ እና በጥገኛ ተህዋስያን የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉት ፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶች፤ በቀድሞ የአወሳሰድ መጠናቸው ተወስደው የበሽታ አምጪ ጀርሞችን ሙሉ በሙሉ መግደል ሲሳናቸው አልያም መራባታቸውን መግታት ሲያቅታቸው ፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶቹ በጀርሞች የመላመዳቸው ምልክት መሆኑ ተገልጿል።

ምክንያቶቹም በህክምና ባለሙያ ከታዘዘው አሳንሶ ወይንም አስበለጦ መውሰድ ወይም መድኀኒቶቹን ማቋረጥ እና መዋዋስ ሲሆኑ፤ ፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶችን የወሰዱ እንስሳት መድኀኒቶቹ ከደማቸው ሙሉ በሙሉ ሳያልቁ የእንስሳት ተዋፅኦ ውጤቶችን መጠቀም በዋነኝነት ተነስተዋል።

ይህም ሰዎች በቀላል በሽታዎች ምክንያት ከሥራ እንዲቀሩ በማድረግ ከዓመታዊ ጥቅል አገራዊ ምርት ላይ ከ አራት በመቶ በላይ ቅናሽ እንዲኖር ምክንያት ሆኗል ሲሉ በኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን መድኀኒት መላመድና መከላከል አማካሪ ወንዴ አለሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ዋጋቸው ከፍ ያለ ውድ መድኀኒቶችን እንዲጠቀሙ ምክንያት ከመሆኑም በላይ እንደ ካንሰር፣ ቀዶ ህክምና እና ንቅለ ተከላ ህክምናዎች ከባድ እና ውስብስብ እንዲሆኑ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

የመለማመድ ሒደቱ ጀርሞች ለመኖር ሲሉ ራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የሚፈጠር ሲሆን ተህዋስያኑ መድኀኒቶቹ በታማሚው ደም ውስጥ እያሉ እንኳን የመራባት ሒደታቸውን በመቀጠል ሰዎች በቀላል በሽታዎች ሳይቀር ሕይወታቸው እንዲያልፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይህም የፀረ ተዋህስያን መድኀኒቶች ከመገኘታቸው በፊት የነበረውን እና ሰዎች በቀላል በሽታዎች ሲሞቱበት የነበረውን ጊዜ ሊያመጣው ይችላል ሲሉም ገልፀዋል።

በአገራችንም የሳንባ ምች (ቲቢ) የአባላዝር በሽታዎች እና ሌሎች በተህዋስያን ምክንያት የሚመጡ የጤና ችግሮች በመደበኛ መድኀኒቶች የመዳን አጋጣሚዎቻቸው ውስን እየሆነ መጥቷልም ይላሉ። እነዚህ በሽታዎች በአፍሪካ በስፋት ተንሰራፍተው የሚገኙ በመሆናቸው፣ ያደጉት አገራት መድኀኒቶቹን ለማምረት እና ጥናት እና ምርምር ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ አይደለም ብለዋል።

ለችግሩ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው መድኅኒትን በታዘዘለት አግባብ አለመጠቀም ጀምሮ ማቋርጥ እና መዋዋስ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው የሚሉት ወንዴ፣ የጤና ባለሙያዎች የመድኀኒት አወሳሰድ እርከኑን ጠብቀው መደኀኒቶችን ማዘዝ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥት ሕጎችን በማዘጋጀት፣ የሕገ ወጥ መድኀኒቶችን ዝውውር ለመቆጣጠር ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም በእየ መድኀኒት ቤቶቹ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድኀኒቶችን መቆጣጠር መቻል አለበት ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here