በሸኔ ታግተው የነበሩ ኹለት ንፁሃን እና አራት የታጣቂ ቡድኑ አባል በወንዝ መወሰዳቸው ተሰማ

0
1330

እሁድ ሐምሌ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል አቦቴ ደገም ወረዳ በአነግ ሸኔ ታጣቂ ብድን ታግተው የተወሰዱ ኹለት ንፁሃን ሰዎች እንዲሁም አራት የታጣቂ ቡድኑ አባላት በወንዝ ተወስደው ሕይወታቸው ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለደ ገልጸዋል፡፡

ንፁሃኑ በታጣቂ ቡድኑ የተወሰዱት ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 20/2015 ሌሊት ጨፌ በተባለች አነስተኛ የገጠር መንደር መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ካገቷቸው ሰዎች ጋር በሽሽት ላይ በነበሩበት ወቅት በአካባቢው ያለን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ኹለት ንፁሃን እና አራት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሞልቶ በነበረው ወንዝ መወሰዳቸው ተገልጿል።

ሆኖም አርብ ሐምሌ 21/2015 በተደረገው አድካሚ ፍለጋ በታጣቂዎች ከታገቱት ሰዎች የአንዱ እና ኹለት የሸኔ አባላት አስክሬን ሊገኝ መቻሉን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና ኦነግ ሽኔ ተብሎ በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በአካባቢው በስፋት መንቀሳቀስ ከጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው ጥቃት አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ታጣቂ ቡድኑ በዞኑ ሥር ባሉ ከግማሽ በላይ ወረዳዎች ከቀን ወደ ቀን እያደረገ ያለው ሰዎችን አፍኖ የመውሰድ እና ገንዘብ የመጠየቅ ተግባር እየተባባሰ መምጣቱን በመጥቀስም፤ “ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለው እያለ መልሶ የኦሮሞ ሕዝብ ሰቆቃ የሆነ የዘራፊዎች ስብስብ ነው።” ብለዋል።

በአካባቢው እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት፣ ልጆችን ማስተማር እና የንግድ ሥራዎችን መከወን ቅንጦት እየሆነ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፤ “ይህ ኹሉ በደል በማህበረሰቡ ላይ ሲፈጸም አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ሳያውቅ ቀርቶ ነው ወይ?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራርያ ለማግኘት ለሰሜን ሸዋ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አለማየሁ ሰንበታ በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here