በወልቂጤ ጅማ መንገድ የታጠቁ ኃይሎች በአሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው ተባለ

0
1034

እሁድ ሐምሌ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከወልቂጤ ወደ ጅማ በሚወስደው መንገድ ጊቤ ሸለቆ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች በተሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን አሽከርካሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም በጊቤ ወንዝ አካባቢ የፖሊስ ልብስ ለብሰው የሚንቀሰቀሱ ኃይሎች፤ በተለይ በምሽት የሚያሽከረክሩ ሹፌሮችን በማሰቆም ገንዘብ አምጡ እንደሚሉና ገንዘብ አንሰጥም የሚሉ ሹፌሮችን የመኪናቸውን መስታወት እንደሚሰብሩ ነው የተናገሩት።

በጊቤ ወንዝ አካባቢ በርካታ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ቢኖሩም እነሱን ተመሳስለው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በመኖራቸው፤ በምሽት የሚያሽከረክሩ ሹፌሮችን የፖሊስ ልብስ ለብሰው በማሰቆም ዘረፋ መፈጸም ከጀመሩ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ጠቅሰዋል።

የፖሊስ ልብስ በመልበስ ተሽከርካሪው እንዲቆም ያዝዛሉ ያሉት አሽከርካሪዎቹ፤ “ሹፌሮችም የመንግሥት የጸጥታ አካላት ናቸ፤ ለፍተሻ ይሆናል በሚል መኪናቸውን ሲያቆሙ በጦር መሳሪያ በማሰፈራራት ዘርፈው ይሰወራሉ።” ብለዋል።

ታጣቂዎቹ በአካባቢው ዘረፋ የሚፈጽሙት የመንግሥት የጸጥታ አካላት በሌሉባቸው አካባቢዎች እየተዟዟሩ መሆኑ እና ለሳምንታት ጠፍተው ከቆዩ በኋላ እንደሚመለሱም ነው የተመላከተው።

ዘራፊዎቹ ተሽከርካሪዎች የጫኑትን ቁሳቁስ ጨምሮ ሹፌሮች የያዙትን ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ከአካባቢው እንደሚሰወሩም ተገልጿል።

ይህን ተከትሎም አሽከርካሪዎች በምሽት ለማሽከርከር ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው በመጠቆም፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለድርጊቱ ትልቅ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሃመድ፤ “ጥቆማው እስካሁን አልደረሰንም፤ ጉዳዩን አጣርተን ማብራሪያ የምንሰጥ ይሆናል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here