በሳምንቱ በ13 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፀጥታ ችግር ተከሰተ

0
703
  • የተወሰኑ ተማሪዎች በረሃብ ራሳቸውን መሳታቸውን ሰምተናል

ቅዳሜ፤ ጥቅምት 29/2012 በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ ግጭት የኹለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ጥቃት ሲሰነዘር እና የትምህርት ስርዓቱም ተቋርጦ ሰንብቷል።

ይህንን ተከትሎ ከሰኞ ኅዳር አንድ እስከ አርብ ኅዳር አምስት ባሉት ቀናት በወሎ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኦዳ ቡልቱ፣ ጅማ፣ መደ ወላቡ፣ መቱ፣ ወለጋ፣ ደንቢ ዶሎ፣ ደብረ ታቦር፣ ኮተቤ እና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያየ መጠን ያለው ግጭት አስተናግደዋል።

የግጭቱ መነሻ የሆነው ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው የመጀመሪያ ግጭት መነሻ ምን እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም፣ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጦ እንዲሁም ሐሙስ ኅዳር አራት 2012 ላይም በዩኒቨርሲተው ውስጥ በድጋሚ ግጭቱ አገርሽቶ እንደነበረ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የግቢው ተማሪዎች ተናግረዋል።

‹‹የሞተ ሰው ስለመኖሩ ባናውቅም ብጥብጥ ግን ነበር፣ መከላከያ ተማሪዎች ወደ ውጪ እንዳይወጡም እየከለከለ ሲሆን ግቢ ያሉ ተማሪዎች ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል›› ስትል አንድ የጊቢው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ተናግራለች።

ስለግጭቱ መነሻ ስታስታውስ፣ ቅዳሜ ሊከሰት ሰኞ ቀን ላይ ‹‹ቅዳሜ ረብሻ ስላለ የትምህርት ማስረጃችሁን አውጡ›› የሚል መልዕክት እንደደረሳቸው እና የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንዲሁም የዶርም አባላቶቿ ሐሙስ ጥቅምት 28/2011 ከሰዓት ግቢውን ጥለው በወልዲያ ከተማ ባሉ አንድ የጓደኛቸው የቅርብ ዘመድ ቤት መጠለላቸውን ትናገራለች።

‹‹እኛ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ስለሆንን ሙሉ የትምህርት መረጃችን በእጃችን ስላለ እሱን ይዘን ራሳችንን አድነናል፤ ነገር ግን ያልሰሙ እና የነበረው ሁኔታም ይረጋጋል በሚል ግቢ ውስጥ የቆዩት እስከአሁን መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል›› ስትል ታስረዳለች። የግቢው ድባብ እና ሳምንቱን ሙሉ የነበረው ሁኔታ ያስታውቃል ያለችው ተማሪዋ፣ ያለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ችግር ተነስቶ እንደነበር አሁንም እንደሚነሳ ከእነሱ ቀድመው የገቡ ተማሪዎች እንደነገሯቸው ትናገራለች።
ግጭቱ በተጀመረበት እለት ቅዳሜም ተመራቂ ተማሪዎች ዳስ ሰርተው ሲጨፍሩ አንደዋሉ የሚገልፀው ሌላ የግቢው ተማሪ፣ ውጤታቸው የተበላሸባቸው ተማሪዎች ግጭቱን ቀስቅሰዋል ሲባል መስማቱን ይናገራል። የአንደኛ ዓመት ተማሪዋ ግን ከግቢው ውጪ የገቡ ሰዎች አሉ የሚል መረጃ በሰፊው ሲሰራጭ እንደሰማች ትናገራለች።

ረብሻው ከተነሳ በኋላ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ግቢው መግባታቸውን የገለፁት ተማሪዎቹ፣ የግቢ ፖሊስ በቁጥሩ በጣም ትንሽ እንዲሁም ግጭቶች ሲነሱም ብዙም ጣልቃ እንደማይገባ ይናገራሉ።

ጅማ
አዲስ ማለዳ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች እና የከተማው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ እሁድ ምሽት ላይ የአማራ ክልል ተማሪዎች ለቀው ይውጡ የሚል ወረቀት መበተኑን ተከትሎ ሰኞ ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ጥቃት ሊደርስብን ይችላል በሚል ፍርሃት ግቢውን ለመልቀቅ ሞክረው ነበር። ተማሪዎቹን ሌሎች ተማሪዎች ‹‹ኀላፊነት እንወስዳለን፤ ተመለሱ ማንም አይነካችሁም›› ብለው ቢመልሷቸውም፤ የተወሰኑት ላይ ጥቃት መድረሱን ተማሪዎች ተናግረዋል።
‹‹ብዙ ተማሪዎች በቤተክርስቲያን እና በመስገጊድ ተጠልለው ያሉ ሲሆን ሐሙስ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ሔደው እንደጎበኟቸው ሰምተናል። የተወሰኑ ተማሪዎች በረሃብ ራሳቸውን መሳታቸውን ሰምተናል›› ሲል አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው ተማሪ ተናገሯል። ወደ ግቢው ገብተው ምግብ ለመመገብ በመፍራታቸው ምክንያት መራባቸውን እና ግቢውም ምግብ ባሉበት ባለማድረሱ መቸገራቸውን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

የጅማ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ከቅርብ ገጊዜ ወዲህ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ውጪ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አለመኖሩን እና የከተማዋ አጎራባች ከተሞችም በተመሳሳይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል።

አምቦ
በሳምንቱ ግጭት ካስተናገዱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከልም አምቦ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃት ተሞክሮ የፌዴራል ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ማክሸፉን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ይናገራሉ።

በአምቦም በተመሳሳይ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሕይወታቸው ያለፈውን ኹለት ተማሪዎች ተከትሎ ኅዳር 3 በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥቂት ተማሪዎች ሰለማዊ ሰልፍ ሲያካሒዱ ነበር። ሰልፉ ወደ ግጭት ተለውጦ ከ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መጀመሩን እና 10 የሚደርሱ ተማሪዎች ቀላል የሚባል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይገልፃል። በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ተማሪዎች በእምነት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን የመማር ማስተማሩ ሒደት ተቋርጦ አንዳንድ ተማሪዎች ወደ መጡበት መመለሳቸውን ገልጾልናል።

በ 2012 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከመግባታቸው በፊት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎች ወላጆችን ተማሪዎችን እና የወረዳዎቹን ተወካዮች ያካተተ ውል ተፈራርመው የነበረ ሲሆን፣ በውሉ ላይም ተማሪዎቹ በብጥብጥ ውስጥም ሆነ በሌሎች አጓጉል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፈው ሲገኙ ለሚወሰድባቸው እርምጃ እራሳቸው ተማሪዎቹ እና ወላጆች ኀላፊነቱን እንደሚወስዱ መጠቀሱን ምንጫችን ገልፀዋል።

‹‹ከግጭቱ ሦስት ቀናት በፊት ተመሳሳይ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ ከዐስር የሚበልጡ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው መባረራቸውን ሰምተናል›› ብለዋል።
ተማሪዎች ፈርመው የገቡት ውል ሚናው ምን ነበር?

በተያዘው ዓመት መንግሥት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለመቀነስ በሚል ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ ተማሪውን ጨምሮ አራት አካላትን ያሳተፈ ውል ማስፈረም ነበር። ‹‹የተማሪዎች እና የግቢ አጠባበቅ ስርአት›› በሚል ስያሜ በተማሪው፣ በወላጆቹ፣ በወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው መካከል የሚፈረም ውል እንደሆነ አዲስ ማለዳ የተመለከተችው ባለ ኹለት ገፅ ቅጽ ይገልጻል።

በወላጅ የሚሞላው ቅጽ እንደሚገልፀው ወላጆች ልጆቻቸው ለሚያሳዩት ያልተገባ ባህርይ ወይም የግቢውን ሕግ እና ደንብ ጥሰው እንዳይገኙ ‹‹የመከርኩ ሲሆን ለሚወሰድበት እርምጃ በሕግ ተጠያቂ መሆኑን እያስገነዘብኩ በፊርማዬ አረጋግጣለሁ›› በሚል ተቀምጧል።

የወረዳ ባለሥልጣኑም ለወላጆች እና ለተማሪው ስላለባቸው ኀላፊነት እና ግዴታ ማስገንዘባቸውን ከመግለጽ ባሻገር የሚጥለው ኀላፊነት የለም። ‹‹ያለ አድልኦ ለማገልገል እና ይህም ተማሪ በሚቻለው ሁሉ ለማገዝ›› በሚል የትምህርት ተቋሙ ተወካይ ፊርማቸውን ያሳርፋሉ።

በውሉ ላይ ሞያዊ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት የሕግ መምህሩ ሚኪያስ በቀለ፣ የውሉን ችግሮች የሒደት እና የይዘት በሚል ለኹለት ይከፍሉታል። ውሉ በተፈጸመበት ወቅት ሕጋዊ ብቃት የሌላቸው (18 ዓመት ያልሞላቸው) ልጆችን ማሳተፉ በራሱ የውሉን ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል ሲሉ ይናገራሉ። አክለውም መሰረታዊ ከሆኑ የውል ሕግ መርሆዎች አንዱ የሆነው የተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ ያለምንም ጫና ፈልገው እና ወደው ያልሰጡበት መሆኑ የሕጋዊነት ጥያቄ ያስነሳል ይላሉ።

‹‹አንድ ወላጅ እና ልጁ ይህንን ውል ካልፈረሙ ልጆቻቸው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ስለማይገቡ ተገደው የሚገቡት ውል በመሆኑ ፈቃድ አልተገኘበትም›› ሲሉም ያብራራሉ።

ውሉ ከሥያሜው ጀምሮ መሠረታዊ የሆነውን የውል ባህሪይ ያልያዘ እና ውል ሰጪ እና ተቀባይ በአግባቡ ያልተለዩበት እንዲሁም በሕግ ፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ግዴታዎች ያልተቀመጡበት ነው፤ እንደ ሚኪያስ አገላለጽ። አንድ ወላጅ ልጁ ከሞተበት በኋላ የትምህርት ተቋሙን ፍርድ ቤት ከሶ ካሳ ለመጠየቅ ቢፈልግ ይህ ውል ላይ የተቀመጠ ግዴታ ያለመኖሩ ሰነዱ ውል ነው ለማለት እንኳን የሚያስቸግር ነው ብለዋል።

አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ ከሰሩበት የሴኔት ሕግ እና የተማሪዎች መተዳደሪ ደንብ የተሻለ አቅም አለው ብለዋል። ነገር ግን እነዚህን ሕጎች ለማስፈፀም የሚስችሉ የዲሲፕሊን ኮሚቴ እና የግቢ የፀጥታ አካላት አደረጃጀት ላይ ግን ለውጥ መደረግ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አደረጃጃትም የፌዴራል ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ አወቃቀሩ ገለልተኛ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ተቋማቱ የፌዴራል እንደመሆናቸው የተሻለ ገለልተኛ በመሆን ግጭቶቹን የሚያረጋጉ የፌዴራል ጸጥታ ኀይሎች ፈጣን ምላሽ እና ጥበቃ ማድረግ አለባቸው።

‹‹የክልል ፖሊሶች ላይ ከፍተኛ ወገንተኛነት እየታየ በመሆኑ ቢያንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ሳያስፈልግ በፌዴራል የጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ማድረግ ይቻላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here