የትምህርት ተቋማት ቋንቋ ትምህርት ብቻ ይሁን!

0
553

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርትና የእውቀት እንዲሁም የጥናትና ምርምር አውድ ናቸው። የትምህርት ስርዓትና ጥራት ይቆየንና ስፍራዎቹ ግን እውቀትን የሚያህል ለሰው ልጅ እድገትና ለውጥ እንዲሁም ዛሬ ላለበት ደረጃ ያደረሰ ሀብት ይገኝባቸዋል። በእነዚህ ተቋማት ሰዎች ተቀርጸው ለራሳቸውም ለአገርም እንዲጠቅሙ፣ ሕይወታቸውም ዋጋና ምክንያት እንዲኖረው ያደርጉ ዘንድ መሠረት ይጥሉበታል።

ኢትዮጵያን ላለፉት 28 ዓመታት በማስተዳደር የቆየው የኢሕአዴግ መንግሥት ከሠራቸውና ከነችግሩም ቢሆን ከሚመሰገንባቸው ተግባራት አንዱ ትምህርትን ማስፋፋት መቻሉ ነው። ይልቁንም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጠረፍ ተብለው እስከተዘነጉ የአገሪቱ ክፍላት ድረስ ተደራሽ ተደርጓል። በቁጥር ደረጃ በቂ ነው የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ባይሆንም ከ50 በላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የመሰናዶ ትምህርታቸውን በሚፈለገው ነጥብ የጨረሱ ተማሪዎችን ይቀበላሉ።

እነዚህ ተቋማት የአገር እንደመሆናቸው መጠን ከኢትዮጵያ አራቱም አቅጣጫ ትምህርትን ፍለጋ የሚወጡ ዜጎችን ያስተናግዳሉ። እነዚህን ዜጎች ታድያ ከየትኛውን ማንነት በላይ የጋራ ሆኖ የሚያግባባቸው ቋንቋ ትምህርትና ትምህርት ብቻ ነው። ለዚህም ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው የሌላ አገር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ተከታለው መጨረሳቸው በቂ ማሳያ ነው።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በጥቅምት ወር መጨረሻ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተከሰተ ‹ግጭት› የኹለት ተማሪዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ይህ ብዙዎችን ያስቆጣና በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ሆኖ አልፏል። ነገሩ በዚያ ያበቃል ተብሎ ቢጠበቅም በተመሳሳይ የሞትና የኹከት ዜና ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ተሰምቷል። ይህም በእጅጉ ልብ የሚሰብርና የሚያሳዝን፤ ለወላጆችም ስጋትን የሚፈጥር ክስተት ነው።

እነዚህን ክስተቶች ተከትሎም የትምህርት ተቋማት የረብሻና የስጋት ቀጠና እየሆኑ ይገኛሉ። መንግሥትም በትምህርት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ‹በእኔ ይሁንባችሁ! አስተማማኝ ይሆናል› ብሎ የማለለት የተቋማቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት ግምሽ ዓመት ሳይጠጋ ተናግቷል። የከፋ ሆኖም የተማሪዎች ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሕይወትም አደጋ ላይ ወድቋል።

ለዚህ መነሻ የሆነውና በተለያዩ ከተሞች ሲታይ የነበረውን ሁከት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያስገባው መዘናጋት ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይም የመጀመሪያው የሞት ዜና በተሰማበት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የሆነው ሁሉ ቀድሞ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ እንደነበር የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጮች ይጠቁማሉ። ይህ መረጃ የደረሳቸው ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎችም ጊቢውን ጥለው እንደወጡ ጭምር ለማወቅ ተችሏል። ተማሪዎች በዚህ ልክ ያወቁትን የጊቢው አመራርና አስተዳደር አያውቀውም ማለት ደግሞ ዘበት ነው።

ከዚህ ባለፈ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የተፈጠረው ክስተት በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሲደገምና ብሔር እየተጠቀሰ፣ ‹‹የእገሌ ብሔር ተወላጅ የሆናችሁ ተማሪዎች ጊቢውን ለቃችሁ ውጡ!›› የሚል ማሳሰቢያ በየጊቢዎቹ ግድግዳዎች ሲለጠፍ ‹‹ማነህ!›› ተብሎ የተወሰደ እርምጃም አልታየም፤ ድምጽም አልተሰማም። እረኛ እንደሌላቸው በጎችም ተማሪዎች እዛና እዚህ ሲበታተኑ፣ በሃይማኖት ተቋማት ሲጠለሉም ‹ማሳሰቢያ› ሰጥቶ ወደ ጊቢያችሁ ተመለሱ ከማለት ውጪ ተማሪዎችን ለማጽናናትና ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ የተደረገ ነገር የለም። በዚህም ቸልተኛነት ምክንያት ተጨማሪ የተማሪዎች ሕይወት መስዋዕት ሆኗል። ይህንንም ክስተት አዲስ ማለዳ አጥብቃ ታወግዛለች።

ከዚህ የሚብሰው ደግሞ ጉዳዩ ምንም ዓይነት ብያኔ ያልተሰጠበት ሲሆን አንዳንዱ ግጭት፣ ሌላው ብጥብጥና ሁከት እያለ የሚጠራው መሆኑ ነው። ይህም ተማሪዎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑና በፍርሃት እንዲተያዩ የሚያደርግ፤ የሥነ ልቦና ጫናውን የሚጨምር ነው። ልጆቻቸውን አምነው የላኩ ቤተሰቦችም ስጋት ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል። ጉዳዩ ላይ በቂ መልስና አስተያየት ከትምህርት ተቋማቱም ሆነ ከመንግሥት ያልተሰጠ መሆኑ ተማሪዎች እርስ በእርስ እየተጋጩ እንደሆነ እንዲታሰብም ያደርጋል።

ይሁንና ከሰሞኑ በወጣ ዜና ደግሞ ተማሪ ያልሆኑና ሐሰተኛ መታወቂያ ይዘው በዩኒቨርስቲዎች የተገኙ ሰዎች እንዳሉ ይጠቁማል። በዚህ መሠረት ጉዳዩ በተማሪዎች መካከል አለመተማመን ለመፍጠርና አገር እንዳትረጋጋ ለማድረግ የሚከናወን ጥቃት መሆኑን ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ተቋማቱም መማሪያ ሳይሆን የፖለቲካ መቆመሪያ ወደ መሆን አዘቅት እየጠለቁ ይስተዋላል።

የኢትዮጵያ ታሪክን አገላብጦ ለተመለከተ በርካታ አመጾች የተነሱት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው። በበርካታ የአገሪቱ ለውጦች ላይም የተማሪዎች ጥያቄና አመጽ ትልቁን ድረሻ ይወስዳል።

ተማሪዎች የተለያየ የብሔር ማንነት ይዘው በአንድ የትምህርት ገበታ መቋደሳቸው ጠባብነት አንደርድሮ ቁልቁል እየወሰዳት ያለችውን ኢትዮጵያን ይታደጋል፤ የተሻለ ስብእናን አግኝተው አገርን ይቀይራሉ ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች ናቸው። እነዚህ ዜጎች በሚሰባሰቡባቸው በእነዚህ ተቋማት የሚደርስ ኪሳራም ተወደደም ተጠላ በአገር እንደሚደርስ ጥያቄ የለውም።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከአምስት ቀናት በፊት በትዊተር ገጻቸው፤ ‹‹የትምህርት ተቋሞቻችን እውቀት ማሳደጊያና የጥልቅ እሳቤ ክህሎት ማበልጸጊያ ናቸው። ተማሪዎቻቸውም ሐሳብን በማፍለቅና በጤነኛ ሙግት የተራራቀ ማህበረሰብ ለማቀራረብ ድልድይ እንጂ የመለያየት ወኪሎች መሆን አይገባቸውም›› ብለዋል። አዲስ ማለዳም በዚህ ሐሳብ በእርግጥ ትስማማለች።

እንደውም ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት በየአጥር ጊቢያቸው ‹አምሳለ-ኢትዮጵያ› የሚባሉና ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተማሪዎችን እንደመቀበላቸው የብዝኀነት ምሳሌ መሆን ይገባቸዋልም ስትል ታምናለች። ስለዚህም መንግሥት በበላይነት፤ የተቋማቱ አመራር ደግሞ እንደ ቅርበቱ ሰላምን በማስከበር ረገድ እያሳዩ ያለውን ቸልተኛነት በመተው በጊቢዎቹ ለሚፈጠረው እያንዳንዷ ኮሽታ፣ ለሚነገረው እያንዳንዱ ቃል ትኩረት በመስጠት አስቀድሞ መፍትሔ ሊያበጁ ይገባል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሏቸውን ተማሪዎች የሚያውቁና በመታወቂያ የሚያስተናግዱ መሆናቸው ይታወቃል። በቁጥር ሳይቀር ለሚታወቁና አምነዋቸው ለሚሔዱ ተማሪዎች ጥበቃና ከለላ ለማድረግ፤ በጊቢዎቹ ውስጥ የሚነገረው ቋንቋ ብሔር ወይም ሃይማኖት ሳይሆን ትምህርት ብቻ እንደሆነም የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው። የተማሪ ሕይወት ማለፍ ይቅርና በጊቢው ውስጥ ለሚጠፉ ንብረቶችም አስተዳደሩ ተጠያቂ መሆን አለበት/ነውም።

በሀሰተኛ መታወቂያ ወደ ጊቢው የሚገቡትን ሆነ ስጋት ቀስቃሽና አዋኪ ማሳሰቢያዎችን የሚለጥፉትን ተከታትሎ የመያዝ ግዴታ የአስተዳደሩ ነው። ጥፋቱን እየፈጹሙ ያሉት ተማሪዎች ይሁኑም አይሁኑም፤ በግልጽ ሊነገርና ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በአግባቡ መምራትና መጠበቅ ለመንግሥት የቤት ሥራ የሚሆነው አንድም አገርን በአግባቡ የመምራት አቅም በጉልህ ማሳያ በመሆናቸው ነው።

በእርግጥ ቀደም ባለው ጊዜ በየክልሉ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የየክልሉ ተወላጅ በሆኑ አስተዳዳሪዎች እንዲመሩ መደረጉ የተቋማቱን ቋንቋ ከትምህርት በማራቅ በኩል ድርሻውን እንደተወጣ ግልጽ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን፤ ይህን ሁሉ አቆይቶ፤ የተፈጠሩ፣ የታዩና የተሰሙ ክስቶችም የተለያዩ ቀለማት እየተቀቡ እኩይ ምግባርና ዓላማ ያላቸው አጥፊዎች ለገዛ ፈቃዳቸው የሚጠቀሙበት እንዳይሆን እውነተኛውና ትክክለኛውን መረጃ ሊነገር ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በትላንትናው እለት ኅዳር 5/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት የዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራሮች፣ ፕሬዚዳንቶች እና ሚኒስትሮች በተገኙበት በወቅታዊ የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ ላይ ባደረጉት ውይይት፤ የሚመለከታቸው ሁሉ በመረባረብ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ወደ መረጋጋት የማይመልሱ ከሆነ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል። የቁጥጥር ስርዓቱን ማዘመንና ማጥበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዚህ መሠረት ከቃል በዘለለ በተግባር በተቋማቱ ማሻሻያዎችን አድርገውና እርምጃዎችን ወስደው በፍጥነት የተቋማቱን ሰላም መመለስ ያስፈልጋል። ተቋማቱ ለፖለቲከኞች መቆመሪያ እንዲሆኑ መፈቀድ የለበትም። ወላጅም ልጁን ወደ ትምህርት በመላኩ ምክንያት አደጋ ላይ እንደጣለውና እሳት ላይ እንደጣደው ሊሰማው አይገባም። ከዚህ በኋላ ቸልተኛነትን በተመው የተቋማቱ ቋንቋ ትምህርት ሆኖ እንዲቀጥል ተማሪዎችና የየአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የተቋማቱ አመራሮች ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here