ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተቀበሩ ፈንጂዎች በአስቸኳይ እንዲጸዱ ተጠየቀ

0
591

ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተቀበሩ ፈንጂዎችን የማጽዳቱ ሥራ በአስቸኳይ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት አሳስቧል፡፡

ኮሚሽኑ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ በጦርነቱ ወቅት የተቀበሩና መሬት ላይ አላግባብ ተበታትነው የሚገኙ ጸረ ሰው ፈንጂዎች፤ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም ጨምሮ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በመግለጫው ጦርነቱን ተከትሎ ንጹሃን ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በእርሻ፣ በውሃ መቅጃ እና በገበያ ቦታዎች እንዲሁም ወደ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች ተቋማት በሚወስዱ መንገዶች አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል ብሏል።

ኮሚሽኑ ይህን በተመለከተ አደረኩት ባለው ክትትል፤ በአፋር ክልል፣ ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት ምክንያት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡

በተጨማሪም ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን እና በአድዓር ወረዳ 23 ሕፃናት በፈንጂ ጉዳት እንደሞቱ እንዲሁም፤ ወደ 20 የሚገመቱ ሌሎች ሕፃናት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መረዳቱን ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ አክሎም፤ በአዲአርቃይ ወረዳ በጦርነቱ ወቅት ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከመደረጉ በፊት አካባቢውን ወዳድቀው ከሚገኙ የጦር መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ የማጽዳት ሥራ ባለመከናወኑ ሕይወታቸው ያለፈ እና አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕፃናት መኖራቸውን ተግንዝቤያለሁ ብሏል።

ስለሆነም ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎችን የማጽዳት እና ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ተግባር ሊፈጠን ይገባል ሲል አሳስቧል።

የተቀበሩ ፈንጅዎችንና የተጣሉ የከባድ መሳሪያ ቅሪቶችን ከማጽዳት ተግባሩ ጎን ለጎንም፣ መንግሥት ለፈንጂ ተጎጂዎች ሊደረጉ የሚገባቸውን የማቋቋም እና ተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎች እንዲያስፋፋ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here