ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የማዕድን ሃብቶች ቢኖሩም ማዕድኑን ለማልማት የሚሆን ልምዱ እና እውቀቱ የለንም ሲል የማዕድን ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክተር አወቀ ተስፋው፤ በኢትዮጵያ ያለውን የማዕድን ሃብት በቂ እውቀት ያላቸው የውጭ የግል ባለሃብቶች ወደ አገራችን ገብተው እንዲያለሙ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አወቀ አክለውም “በአገር ውስጥ ያለውን የማዕድን ሀብትን ለማበልጸግ የሚያስችል ሰፊ ጥናት ቢጠናም፤ ተግባራዊ ለማድረግ አስቻይ አቅም እና ልምዱ ባለመኖሩ ወደ መሬት ሳይወርድ ቀርቷል፡፡” ያሉ ሲሆን ነገር ግን አሁንም የፍለጋ ጥናቱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
እንደአብነትም፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል አንዱ ሲሆን፤ በክልሉ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም በጎጃም በርካታ የማዕድን ሃብቶች ተከማችተው እንደሚገኙ በመጠቆም፤ “ማዕድኖችን ጥቅም ላይ ለማዋል የውጪ የግል ባለሃብቶችን እያስገባን ነው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የማዕድን ሃብት “በመንግስት ብቻ የሚለማ አይደለም፤ የግል ባለሃብቱን ሚና ይፈልጋል” ያሉት ሃላፊው፤ “ሃብቱ እንኳን ቢኖረን ልምዱ እና እውቀቱ የለንም፡፡” በዚህም ያለንን የማዕድን ሀብት ለማልማት እንቀፋት ሆኖብናል ብለዋል፡፡
መንግሥት ማዕድኑን ለሚያለሙ ባለሃብቶች የመንገድ እና የመብራት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እገዛ ያደርጋል እንጂ የፋይናንስ አቅም የለውም ሲሉም አክለዋል፡፡
የውጭ የግል ኩባንያዎች በቂ የቴክኖሎጂ እውቅት እና ማዕድኑን ለማልማት የሚያስችል በጀት ሰላላቸው በዘርፉ ተሰማርተው እንዲሰሩ ፈቃድ እየሰጠን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ስምንት ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል እያመረቱ መሆኑን እና ከስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ከደቡብ ሱዳን ሲገዛ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ማምረት መጀመሯን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የውጭ ኩባንያዎች የማዕድን ሃብቱን ለማጥናት የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎች ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደጋፍ እያደረገ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡



