ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከባለፉት ኹለት ወራት ጀምሮ በዞኑ ሥር ከሚገኙ 11 ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት ኹለቱ ብቻ መሆናቸውን የደምቢ ዶሎ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የደምቢ ዶሎ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሌሊሳ አያና ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ የዞኑን ዋና ከተማ ደምቢ ዶሎን ጨምሮ ዘጠኝ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ ያሉት ጊዳሚ እና ሀሮሲቡ ወራዳዎች በጊምቢ ከተማ በኩል ከሚመጣው ዋናው የኃይል ማሰራጫ መስመር ስለሚያገኙ ነው ያሉት ኃላፊው፤ “የዞኑን ዋና ከተማ ደምቢዶሎን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ ለተቋረጠባቸው ዘጠኙ ወረዳዎች ከጊምቢ ከሚመጣው ማስተላለፊያ መስመር እንዲዘረጋላቸው በተደጋጋሚ የጠየቅን ቢሆንም መፍትሄ አልተገኘም፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።
ችግሩ የጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት መሆኑን በመግለጽም፤ እየተቆራረጠም ቢሆን የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በዘጠኙም ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ ከተረቋጠ ኹለት ወር አልፎታል ነው ያሉት።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ጋምቤላ ክልል መሆኑ እና የኤሌክትሪክ መስመሩን ከጋምቤላ ክልል ጋር እንደሚጋሩ ጠቅሰውም፤ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የእንጨት ፖሎች ለረዥም ጊዜ አገልግሎት በመስጠታቸው ማርጀታቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል፡፡
“የኃይል የማስተላለፊያ መስመሩ የተዘረጋው በደርግ ዘመነ መንግሥት በ1980 ነው፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ “36 ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ይህን ያህል ዓመት ምንም ዓይነት እድሳት ተደርጎለት አያውቅም፡፤” ሲሉም ጠቁመዋል።
የእንጨት ፖሎቹ ወደ ብረት እንዲቀየሩ ለከተማ አስተዳደሩ እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም መፍትሄ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ እስካሁን ከስልሳ በላይ ፖሎች ወድቀዋል ብለዋል።
በአንጻሩ ከጋምቤላ ወደ መቱ የሚሄደው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎች ከእንጨት ወደ ብረት የተቀየሩ በመሆኑ አገልግሎቱን በአግባቡ እያገኙ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ የከፋ በመሆኑ፤ ያሉትን እንኳን አድሶ በተወሰነ መልኩ ወደ ሥራ ለመመለስ እንዳተቻለ ነው ኃላፊው የገለጹት።
በሌላ በኩል “የማሰራጫ ጣቢያው ጋምቤላ መሆኑ የእድሳት ሥራውን ለመስራት የግድ የጋምቤላን መንግሥት ፈቃድ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ይህ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የቄለም ወለጋ ዞን አሥተዳዳሪ ገመቹ ጉርሜሳ በበኩላቸው፤ “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደጋጋሚ ብናወራም ቃል ከመግባት እና ይስተካከላል ከማለት በዘለለ የተሰራ ሥራ የለም፡፤” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው አክለውም፤ በዞኑ ያሉ ጤና ተቋማት፣ ትምርህርት ቤቶች፣ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን በማንሳት፤ አሁንም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አፅንዖት እንዲሰጡበት አሳስበዋል፡፡
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኝት ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደወለች ሲሆን፤ ተቋሙ ከእኔ ይልቅ ጉዳዩ የበለጠ የሚመለከተው የኦሮሚያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ሆኖም የክልሉን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡



