በጅማ ዞን የመንግሥት አመራርና የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ አንድ ሰው መገደሉ እና 10 ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ

0
404

ረቡዕ ነሐሴ 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሰጠማ ወረዳ ሰኞ ነሐሴ 08/2015 በጅማ ዞን የመንግሥት አመራርና የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ፤ አስር ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

ድርጊቱ የተፈጸመው የወረዳው አስተዳደር የአካባቢው ማህበረሰብ ለዘመናት ሲጠቀምበት የኖረውን የግጦሽ እና የእርሻ መሬት ባለይዞታዎቹን ሳያወያይ ለኢንቨስትመንት በሚል ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠቱን ተከትሎ፤ በማህበረሰቡ እንዲሁም በፖሊስና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ነው ተብሏል።

በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ደርጊቱን ለማውገዝ በዕለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፤ የሰጠማ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሚስባሁ ያህያ ከፖሊስ አባላት ጋር ወደ ሰልፉ ቦታ ማቅናታቸው ነው የተገለጸው።

ሆኖም አስተዳዳሪው ሰልፍ ለወጡት ነዋሪዎች ጉዳዩን ለማስረዳት በሚሞክሩበት ወቅት ተቃወሙ ባሰሙ ወጣቶች ላይ ፖሊስ እና ራሳቸው የወረዳው አስተዳዳሪ የተኩስ እሩምታ በመክፈት አስር ሰዎችን ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ግለሰቦች መካከል የአንድ ወጣት ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን በመግልጽ፤ ቀሪዎቹም በአሳሳቢ ኹኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት እንዲሁ “ቦታው ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል” በሚል ከፍተኛ ተቃሞ ተከስቶ እንደነበር የገለጹት የዓይን እማኞቹ፤ በወቅቱም ከጸጥታ አካላትና ከወረዳው አመራሮች ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ ጉዳዩን የተቃወመው ልማትን የሚቃወም ሆኖ ሳይሆን፤ አሰራሩ ህጋዊ ባለመሆኑ ነውም ተብሏል።

ነዋሪዎቹ እስከ ክልል ድረስ ሄደው አቤቱታቸውን ያቀረቡ ቢሆንም መፍትሄ ማግኘት አለመቻላቸውም ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ በዞኑ በአጋሮ ከተማ ነሐሴ 07/2015 ኹለት የከተማው ወጣቶች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ደረሶባቸው ሕክምና ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመንግሥት የጸጥታ አካላት እና አመራሮች በንጹሃን ላይ እየፈጸሙት ያለው የመብት ጥሰት እየተባባሰ ነው ተብሏል።

የሰጠማ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሻቡ ቃድሬ መሬቱ 2 ሺሕ ሄክታር ስፋት እንዳለው እና ባለቤትነቱም የመንግሥት እንጂ የግለሰብ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ “ሰኞ ዕለትም በሰዎች ላይ ሞት እና ጉዳት መድረሱ እውነት ነው።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“ሆኖም ጉዳቱ የደረሰው ነዋሪዉ የተለያዩ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን በመያዝ በወረዳ አስተዳዳሪ እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሞክሩ በተከፈተ ተኩስ እንጂ፤ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት የለም።” ብለዋል።

መሬቱም በኢንቨስትመንት ለባለሀብቶች ተላልፎ እንዲሰጥ ከክልል እስከ ወረዳ መግባባት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ የአካባቢው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ በሚያቀርቡት ተቃውሞ ተላልፎ አልተሰጠም ሲሉ ተደምጠዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here