እስራኤል በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተእስራኤላውያንን ጉዳይ የሚከታተል ልዩ መልዕክተኛ ሾመች

0
400

ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የእስራኤል መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ወገኖች የሚያነሱትን ቅሬታ የሚከታተልና የመፍትሔ ጉዳይ የሚያቀርብ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙ ተገልጿል።

የእስራኤል አሊያህ እና የውህደት ሚኒስቴር በኩል የተሾሙት ልዩ መልዕክተኛው ኢትዮጵያን በተመለከተ የእስራኤልን ወቅታዊ የስደት ፖሊሲ የሚገመግም ቡድን እንዲያዋቅሩ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ከአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይሁንታ በመጠባበቅ ላይ ያሉት ተወካዩ፤ የጥናት ቡድኑ በተለይም በአዲስ አበባ እና በጎንደር ወደ እስራኤል ለማቅናት በሚጠባበቁ ቤተ እስራኤላውያን የኢሚግሬሽን ፈተናዎች ላይ እንደሚያተኩር እንዲሁም የጥናት ግኝቱን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያቀርብ እየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተእስራኤላውያንን ጉዳይ በቅርበት በመከታተል ጉዳዩን ለአገራቸው መንግሥት እንዲያሳውቁ የተወከሉት ብርጋዴር ጄኔራል ሃርል ክንፎ ከዚህ ቀደም በእስራኤል ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ላይ ተመድበው ሲሰሩ መቆየታቸውም ተጠቅሷል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችና የአይሁድ ፍልሰት ተሟጋቾች እየሩሳሌም በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ደጃፍ ተሰባስበው፤ ወደ እስራኤል ለመግባት በሚጠባበቁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

በጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኙ ጣቢያዎች ወደ እስራኤል ለመሄድ ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ 4 ሺሕ 226 ቤተእስራኤላውያን መኖራቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በተለይም እንደ ጎንደር ባሉ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ስጋት ወደ እስራኤል ለመጓዝ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖባቸዋል ነው የተባለው።

የእስራኤል መንግሥት በኢትዮጵያ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያንን በሙሉ ወደ እስራኤል አምጥቻለሁ ቢልም፤ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የእስራኤል መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here