“መቼም የትም እንዳይደገም!”

የተዘነጋው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዝየም የረሳነው አላማውን ወይስ ሙዝየሙን?

0
802

“የፊውዳሉ አስተዳደር አንገሽግሾኛል፣ አገር የአንድ መደብ ብቻ የሚዘውራት አይደለችም በሚል ለጭቁኖች ድምጽ፣ ለተበደሉት ፍትህን ሊያሰፍን ወደፊት የመጣው ወታደራዊ ስብስብ የወቅቱን ንጉስ አጼ ኃይለስላሴን “ጃንሆይ ከዚህ በኋላ ለጤናዎም ጥሩ ስላልሆነ ስልጣኑም ይብቃዎት” በሚል ነበር ንጉሱን ያስወገደው።

ይሄው አስተባባሪ ኮሚቴ መስከረም 1967 ጃንሆይን ከስልጣን አውርዶ መንግሥቱ ሃይለማሪያምን ሊቀምበር አድርጎ ሾመው።

የዘውዳዊውን አገዛዘ በመቃወም ወደፊት በመምጣት መንበሩን የጨበጠው ደርግ ለውጥ ከብቀላ የሚጀምር ይመስል 60 የቀዳማይ ኃይለስላሴ ሚኒስተሮችን በመረሸን የቀዳሚ የሥራ ወራቱን አሃዱ አለ።

“ያለ ምንም ደም” ብሎ የኢትዮጵያን እንከን ሊያወድም የተነሳው መንግሥት ታዲያ በመንግሥትም እና መንግሥት በጽኑ ይሞግቱኛል ባላቸው ቡድኖች መካከል በሚደረግ ሽኩቻ ኢትዮጵያ ደምታ በማታውቀው ልክ ደማች፣ ጎዳናዎች በተማሪዎች፣ በወጣቶች፣ በታዳጊዎች ደም ጨቀዩ፣ ምድሪቱ በወላጆች እንባ ረሰረሰች።

ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር በሚል ኹለት ጎራ ብዙዎች ተቀጠፉ፣ በርካቶች አገር ጥለው ተሰደዱ፣ እልፎች ብዙ መስራት አገርን ማገልገል በሚችሉበት አቅም የአልጋ ቁራኛ ሆነው የአገር ሸክም ሆነው ቀናቸውን እንደገፉ ከዓለም ተለዩ።

በአገሪቱ የነበረው የእስረኛን ቁጥር በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ቁጥሮች ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳን ለያኔው አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ለነበራት ኢትዮጵያ ቀርቶ አሁን ህልቆ መሳፍርት ለሆነው ቁጥር እንኳን እጅግ ብዙ ነበር።

በጊዜው የነበሩ ቀበሌዎች፣ ወታደራዊ ካምፖች፣ ፋብሪካዎች እና ቤተመንግሥቶች ወደ እስር ቤትነት፤ ማሰቃያና መረሸኛነት ተቀይረው ነበር። የእስር ቤቱ ዙሪያዎችም በጥርብ ድንጋዮች የተሰሩ ነበሩ። እንዲሁም 5 በ4 የሆኑ እስር ቤቶች ዉስጥ 500 ያህል ሰዎች ታጉረው የስቃይ ሕይወት ይገፉ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከዛ አስጨናቂ ስፍራ እና ከሞት ደጅ በአምላክ እርዳታ ተርፈው ትናንታቸውን የሚተርኩ ሰዎች ዛሬም ይመሰክራሉ። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል መሰረት ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሰዎች መሞታቸውን መገደላቸውን የሚያሳይ ሪፖርት የወጣበት ደርግም “ያለ ምንምን ደም” ብሎ ጀምሮ ደም በደም ካደረገ በኋላ በትጥቅ ትግል ለመጣው ኃይል ስልጣኑን አስረክቦ በየአቅጣጫው ተበተነ።

ተተኪው ኢሕዴግ “በቀል አያስፈልግም የሚሻለው ፍትህ ነው” በማለት 5 ሺሕ ያህል በደርግ ወቅት በተለያየ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን ላይ ክስ በመመስረት 51 ያህሉን በሞት ከቀጣ በኋላ ሌሎች የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እና ከ 20 እስከ 25 ዓመት እስራት እንዲቀጡ አድርጓል።

የፍትህ እና ተጠያቂነቱ ጉዳይ ከተጠናቀቀ በኋላ ታዲያ፤ “በሕይወት ለታጡት፣ በወንድሞቻቸው ቃታ ለተሰውት ሰማዕታት ሃውልት ይቁምላቸው” ተባለ፡፡ ከዛም ሙዝየም ይሁን በማለት ፋሲል ጊዮርጊስ የተባሉ አርክቴክት ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ማለትም ዋና ሙዝየሙ፣ ቤተ መጻህፍት፣ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የስዕል ጋለሪ እና የመጽሃፍት መሸጫን ያካተተ መሆን አለበት በሚል ሃሳቡንም ንድፉንም በራሳቸው ተነሳሽነት ከወኑት።

በአፍሪካ ጎዳና መስቀል አደባባይን ተወስኖ የተገነባው የትናንቱ እውነት፣ ለዛሬ እና ነገ ደግሞ ታሪክ የሆነው ሙዚየም፤ በርካታ ትናንታዊ እውነታዎችን እንዲገልጽ ተደርጎ ነው የታነጸው። የሙዝየሙ ዉጫዊ ገጽታ በጥርብ ድንጋይ የተገነባ ሲሆን፤ ይህም በወቅቱ የነበሩት እስር ቤቶች የነበራቸውን ገጽታ ለማመላከት ነው።

እንዲሁም በሙዚየሙ መግቢያ ደጅ ላይ በግሩም ሁኔታ የተቀረጸው ሐውልት ቀልብን ይስባል፤ ትናንትን አስናፍቆ ሆድ ያስብሳል። አንዲት እናት በእጆቿ ጃኬት የያዘች በግራና በቀኟ ኹለት ሴቶች እራሳቸውን እሷ ትከሻ ላይ ዘንበል አድርገው ይታያል። ከሃውልቱ ሥር “መቼም የትም እንዳይደገም” የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል።

ይህን ሙዝየም ለማሰራት በርካቶች ተረባርበዋል። የገንዘብ ማሰባሰቡ ሂደት ላይ ሰፊ አስተዋጾ ያደረጉት አይነ ጽጌ (የዕውቁ ፖለቲከኛ የአንዳርጋቸው ጽጌ ታናሽ እህት) ወደ ተለያዩ ባለ ሃብቶች ጋር በመሄድ አላማቸውን በማስረዳት ገቢ ማሰባሰቡን በግንባር ቀደምትነት መርተውታል። ከትላልቅ ባለሃብቶች ባለፈም እናቶች መቀነታቸውን ፈተው መጽናኛ ይሆነናል በማለት አግዘዋል።

የቀይ ሽብር ሰማእታት ሙዝየም በየካቲት 28/2002 ከ400 በላይ አባላትን የያዘ በቀይ ሽብር ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሲታገሉ በፖለቲካዊ አመለካከትና እምነታቸው ብቻ በደርግ መንግሥት ለተጨፈጨፉት ሰማዕታት ዜጎቻችን ኹሉ መታሰቢያ” ሙዝየም የሰማዕታቱን ቤተሰብ በመወከል በአንድ ለሊት አራት ልጆቻቸው በተገደሉባቸው እናት ከበቡሽ አድማሱ የክብር እንግዳ ሆነው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተከፈተ።

ከበቡሽ ባለቤታቸው የደርግ መቶ አለቃ የነበረ በወቅቱ ግን ስልጣን የለቀቀ ግለሰብ እሱን ለመበቀል እና በራሪ ወረቀት ትሰጣላቹ በማለት 8፣ 10፣ 12 እና 13 እድሜ የሆናቸውን ልጆቻቸውን ፊት ለፊታቸው ገድለዋቸዋል።

“በአንድ ሌሊት የወለድኳቸው ይመስል በአንድ ሌሊት ጨረሷቸው” ሲሉ በአንድ ሌሊት አራት ልጆቻቸውን ያጡት እናት ቃል የድርጊቱን አስከፊነት፣ ስሜቱን፣ ብሶቱንና ሥቃዩን ገልጸውታል።

አክለውም “እኔ ብቀብራቸው የቤተክርስቲያን ጓሮ ነው፡፡ አሁን ግን የአለም ሕዝብ ነው ልጆቼን የሚጎበኝልኝ” ሲሉ የእናትነት ርህራሄው ዛሬም በሚነዝር ስሜት ይናገራሉ።

በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዝየም የቀይ ሽብር ሰለባዎች አልባሳትና መጫሚያዎች፣  የተለያዩ አይነት መሳሪያዎች እንዲሁም የኢህአፓ ወጣቶች በድብቅ ዲሞክራሲያን የሚያትሙበት መሳሪያ ዳምጠው/ አደፍርስ የሚባሉ መሳሪያዎች ይገኛሉ።

በጊዜው ይታተሙ የነበሩት መጽሄቶችም ዲሞክራሲያ፣ ነጻነትና ትግላችን የመሳሰሉት እንዲሁም በራሪ ወረቀቶችን በሙዚየሙ ታሪከን ሊነግሩ ተቀምጠዋል።

ሌላው የብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጉርድ ፎቶዎች በግድግዳዎቹ ላይ ከነሥሞቻቸው ተቀምጧል፡፡

መኮንን ተፈራ፣ ጌታቸው ገቢሣ፣ ደጉ ደበሌ፣ ትብለጥ ምህረትአብ፣ተዘራ ተክለሚካኤል፣ ኃይሉ ተክለፃድቅ፣ አድነው ከየሮ፣ ሽጉጤ አለሙ፣ ኦሪኦን አያልነህ፣ አሮንተኬ፣ ፉአድ ኢብራሂም፣ ካሣይ ወልደማርያም፣ መሃመድ ከማል፣እንድሪስ ሁሴን፣ ኡመር አብደላ፣ ንጉሴ አሥገዶም ብዙ ሥሞች ብዙ ወጣቶች……!

ሌላው፤ የሰማዕታቱ አጽሞች በመስታወት ተቀምጠዋል የሟቾች ቤተሰቦች እየመጡ አበባ ያስቀምጣሉ።የሟቾች አጽም ከተሰደረበት ፊት ለፊት “ለአገር ይሻል ብለን የተለየ በማሰባችን በእስር ቤታቸው ሲኦልን አሳዩን፣ በጅምላ ጨፍጭፈው ጸሃይ ላይ አሰጡን፣ እንደ አራዊት በጫካ ቀበሩን፡፡ ግን እኛ ብንሞትም ትግላችን አልሞተም ታሪካችንም ከመቃብራችን በላይ ለዘላለም ህያው ነው።” የሚል ጽሑፍ ይነበባል፡፡ የተጻፈውም በጎንደር ከተማ ያለፍርድ የተገደሉ ሰማዕታት የተቀበሩበት ቦታ ላይ እንደሆነም ይገልጻል።

“ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ተብሎ የተጀመረ ለውጥ ምናልባትም ወርቃማ ከሚባሉ ዘመናት የሚመደቡ ዕንቁ የአገር ልጆችን የነጠቀ ሲሆን፤ ከአጠገቡ ወንድሙን፣ እህቱን፣ እናቱን፣ አባቱን፣ ይህንን እንኳ አላየሁም ቢል የትምህርት ቤትና የሠፈር ጓደኞቻቸውን፣ ዕልፍ ሲል ጎረቤቱንና ቢከፋ ዘመዱን ያላጣ ሰው የለም።

የሙዚየሙ አሁናዊ ገጽታ ምን ይመስላል? የረሳነውስ ምኑን ነው?

ሚያዝያ 24/2014 በኢድ በዓል ሰላት ላይ በተፈጠረ ግጭት ጉዳት የደረሰበት ይህ ሙዚየም መስታወቶቹ እንደተሰባበሩ፣ መሰረተ ልማቶቹ እንደተጓደሉ ዓመት ተሻግሮ አሁንም በጉዳቱ እንዳለ ነው። ተዘንግቷል ቢባል ቃላት ያንሳሉ። ትልቅ መልዕክትን የሚያስተላልፈው፣ የትናንት ጠባሳን ዛሬ ላይ እንዳይደገም በዝምታው የሚወተውተው ይህ ሙዚየም ዞር ብሎ የሚያየው ባለመኖሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

በእርግጥ ከሙዚየሙም ባሻገር መልዕክቱም የተዘነጋ በሚመስል አኳኋን “ዛሬም እንዳይደገም” ያልነው ጠባሳ አዲስ ቁስል ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም ወንድም ወንድሙን ይቀጥፋል፣ እናቶችም እምባቸው ከዘመን ጅረት ጋር ተገምዶ ዛሬም ይፈሳል።

በተጠቀሰው ቀን ያጋጠመው ጉዳት የሙዚየሙ ውጫዊ ክፍል የተሰባበሩ መስኮቶችና በሮች ሳይጠገኑ እንዲሁም በዉስጥ በኩል የሚገኙት ጉዳት የደረሰባቸው ግድግዳዎች ሳይጠገኑ አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ያህል ተረስተዋል።

ይህን ሙዝየም እየመጡ የሚያዩት እናቶች አሁንም አሉ፡፡ የትናንት በልጆቻቸው መሞት የተነጠቀውን ተስፋቸውን የሚያለመልምላቸውን ሃውልቱን በነጠላቸው የሚጠርጉት፤ ዉጪ የሚኖሩ የሰማዕት ቤተሰቦች ሲመጡ ደግሞ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ለብዙዎች መታሰቢያነት ብሎም ከታሪክ እንማር ዘንድ የተሰራ ሙዝየም ከተዘነጋ አንድ ዓመት ከሦስት ወር አለፈው። “ሆነ ተብሎ ትኩረት ከተነፈገው ደግሞ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡” ሲሉ ደግሞ አዲሰ ማለዳ በስፍራው በተገኘችበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ ሰራተኞች ተናግረዋል።ወደ ሙዝየሙ መግቢያ በሩ ጋር የቆሙት የመንግሥቱ ሃይለማሪያም መኪና እና ለሰራተኞች ስርቪስ እንዲሆን ከበጎ አድራጎት ድርጅት የተሰጠው መኪና ሳይጠገኑ፣ በውስጥ ያሉት መብራቶች አገልግሎታቸውን ካቋረጡ እንዲሁም የሲኒማ ቤት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ቤት ቆሻሻና የሸረሪት ድር ከወረረው አንድ ዓመት ከሦስት ወራት በላይ ሆኖታል።

የሙዝየሙ የዉሃ መስመር ስላልተከፈለ ቆጣሪው ተነስቷል፣ የሙዝየሙ የላይኛውና የጀርባ ክፍል ተሰነጣጥቆ ዉሃ ያስገባል ግን ማንም ሃላፊነት ወስዶ ነገሮችን ለማስተካከል እንዳልሞከረ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ።

በዚህም ብቻ አይበቃም! ሙዝየሙ “ለገቢ ምንጭ” ብሎ ያከራያቸው ካፍቴሪያው እና የመጽሃፍ መሸጫው ኪራይ መክፈ አላቋረጡም ግን ደግሞ ከኪራይ የሚገኘው ገቢ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚውል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በጊዜው ሙዝየሙ ያከራያቸው ሱቆችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በፍጥነት ማስተካከል የቻሉ ሲሆን ሙዝየሙ ግን ጉዳት ደርሶበትም ያልተቋረጠ ቢሆንም የደረሱ ጉዳቶች ላይ ግን ምንም አይነት እድሳት ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።

“ጉዳቱ በደረሰበት ሰዓት አንዲት የአሜሪካ አምባሳደር ሙዚየሙን ለማየት እና ድጋፍ ለማድረግ በቅድሚያ የኢምባሲው ሰራተኞች ሰዎች በቦታው ተገኝተው ስለ ሙዚየሙ ሊያናግራቸው የሚችል ሰው በማጣታቸው አምባሳደሯ እንዳይመጡ አሳውቀው ተመልሰዋል” ሲሉ አዲስ ማለዳ በስፍራው በተገኘችበት ወቅት ከማዕከሉ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

መረጃ ምንጫችን አክለውም፤ “ከመሄዳቸው በፊት አንዱን ከኢምባሲ ተልከው ከመጡ ሰዎች ውስጥ ጠጋ አልኩትና “ቢመጡ ምን ነበር የሚያደርጉት?” ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም “ቢያንስ አንድ ሚሊየን ብር እንደ ቀልድ ነው ያጡት” ብሎ እንደመለሰላቸው ተናግረዋል።ሙዝየሙ በፊት ከ 30 በላይ ሰራተኞች የነበሩት ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት 15 ሰራተኞች ብቻ ቀርተውታል። ለሰራተኞቹ የሚከፍለው ደሞዝ በጣም አነስተኛና ምንም አይነት ጭማሪ የለውም፡፡ ለአብነትም በድርጅቱ ከ7 ዓመታት በላይ የቆየ ሰራተኛ በገባበት ጊዜ ይከፈለው የነበረው ደሞዝ ነው አሁንም የሚከፈለው።

“በተጨማሪም አመራር ላይ ያሉት ግለሰቦች አንድ ሰራተኛ መብቱን ከጠየቀ “ለምን ካለ” ከሥራው እንዲለቅ በተለያየ መንገድ ግፊት ይደረግበታል፡፤” ሲሉም ምንጮች ጨምረው አስታውቀዋል።

“ይሄ ዘመናዊ ባርነት ነው ለ9 ዓመታት በ1300 ብር ደሞዝ ነው የሰራሁት። የጥበቃ ልብስና ጥቅማ ጥቅም በልመና ነው ከጠየቅን ዓመት በኋላ የሚሰጠው አመራሮቹ የራሳቸው ጥቅም እስከተጠበቀ ድረስ ምንም አይነት አዲስ ሃሳብና ጥያቄ መቀበል ፈጽሞ አይፈልጉም።” በማለት አንድ በሙዝየሙ ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተማረ ሙዝየሙን በአግባቡ ሊያስተዳድር የሚችል የሰው ሃይል አለመኖሩ እና ሙዝየሙን እንደራሱ ሃብት፣ እንደ አገር ሃብት እንደ ሰማዕታት መታሰቢያነት የሚያስብ ባለመኖሩ የመስቀል አደባባይ አዲስ ፕላን ሲወጣ “የሙዝየሙ ካርታ የለንም” በማለት ሙዝየሙ የነበረውን 50 መኪኖችን ማቆም የሚችል የፓርኪንግ ቦታ እንዲሁም የክልሎች ባንዲራ የሚቆምበት ቦታ ሊወሰድበት ችሏል።

ለሙዝየሙ እንዲሁም ለቀይ ሽብር ሰማዕታት ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች ከዉጭ አገራት የሚላከው እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለሙዝየሙ የሚገባው ገንዘብ የተጎጂ ቤተሰቦች በወር በወር ይወስዳሉ። ያንን ገንዘብ አንድ ግለሰብ የ15 እስከ 20 ሰዎችን ፈርሞ የሚወስድበት ሂደት መኖሩንም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

“ታሪክን እያጠፉ ታሪክ መስራት ይመስላል። የቤተ-መንግሥት ያህል የሚከበር ቦታ ነበር ይሄ ከአምስት ዓመት ወዲህ ለፎቶ መነሻ የሚሆነው ቦታ ዛሬ ሳሩ አድጎ ዞር ብሎ የሚያየው አጥቷል። የሙዝየሙ ጎንና ጀርባ የሽንት መሽኛና ቆሻሻ መጣያ ሆኗል። መንግሥት አይፈልገውም፤ አልያም ረስቶታል።” ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

በሙዝየሙ የላይኛው ክፍልም አንድ ቤተ መጻህፍት ይገኛል፡፡ በዉስጡም ብዙ የታሪክ እንዲሁም ሌሎች መጽሐፍት  የያዘ ሲሆን፤ ከአምስት ዓመታት በፊት እንደተዘጋ ቀርቷል። ለምን እንደተዘጋም አይታወቅም።

ከ 15 ቀናት በፊት አንድ ድርጅት ለቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዝየም አድሳት በሚል ገንዘብ ይሰበስባል የተሰበሰበው ምንም ያህል ይሁን መስታወቱን ብቻ ሊያሰራ ተስማምተው የፊተኛው መስታወት ተሰርቷል።

በዚሕ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ቱሪዝም ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የጠየቀች ሲሆን፤ “ሙዝየሙ የራሱ የሆነ አባላትና ቦርድ አለው” ሲል ሚኒስቴሩ ምላሽ ሰጥቷታል፡፡ ከነሱ በተጨማሪ ይሄ አዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮን ነው የሚመለከተው የሚልም ምላሽ አግኝታለች።ሌላው የሙዝየሙ አስተዳደር “ከዚህ በፊት ለሌላ ሚዲያ የቦርድ አባላቱ መረጃ ሰጥተናል! ከዛ የተለየ ምንም የተለየ መረጃ የለኝም፡፡ ይቅርታ ምንም ማድረግ አልችልም” ሲሉ አዲሰ ማለዳ ለጉዳዩ ምላሽ ለመጠየቅ ያደረገችውን ሙከራ በአጭር እንዲቀጭ አድርገውታል።

በተጨማሪም የቦርዱ ምክትል ሊቀመንበር “ከቦርድ አባላት ጋር ተነጋግረን ነው ምላሽ የምንሰጠው፡፡ ነገር ግን ከሥራ አስኪያጁ በኋላ ነው ቦርዱ መረጃ መስጠት ያለበት፤ ግን ይሄንን አደረግን ቢባል እንኳን እኛ ምን እንጠቀማለን። ብዙ ችግሮች ነው ያሉብን ሦስት ጊዜ ተስብሮብናል ማንም ዞር ብሎ አላየንም መንግሥትም ሆነ የትኛውም ሚዲያ አልጠየቀንም። ለሚመለከታቸው ኹሉ አሳውቀናል ምንም የተደረገ ነገር የለም አሁንም በራሳችን ነው የፊተኛውን መስታወት ያሰራነው።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መንግሥትም ሕዝብም አባላቶቹም ትኩረት የነፈገው ለሙዝየሙ ብቻ አይደለም፡፡ ለተቋቋመበት አላማም ጭምር ነው። በዉስጥ ለውስጥ የሚሰሩ ብልሹ አሰራሮችን፣ ስርቆትን፣ በደልን፣ ኢ-ፍትሃዊ አሰራርን፣ ያዩትን የታዘቡትን ሊናገሩ ፈልገው ሰሚ አጥተው ዝም ያሉትንም ጭምር ነው ችላ የተባሉት።

“መቼም የትም እንዳይደገም” ሲሉ እናት ልጆችዋን እና ባሏን አጥታ እንዳታለቅስ፣ አባት ያለጧሪ ቀባሪ እንዳይቀር እህት መከታ እና ጋሻ ወንድሟን እንዳታጣ ነበር። ያለፈው ትውልድ ለአሁን ትውልድ የጦርነት አስከፊነትና አሰቃቂነትን ለማሳየት ነበር።

ይሄ ድርጊት በኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በአለም እንዳይደገም ትምህርት ይሆናል ተብሎ ነው።

ጦርነት በሃሳብ እንጂ በመሳሪያ አይሁን በእናሸንፋለን እና እናቸንፋለን በወዛደር እና ላብአደር የቃላት ልዩነት አንጣላ። ያኔ ሲጀመር መጀመሪያ የሃሳብ ልዩነት ነበር ቀጥሎ ሃይለቃል ነው መጨረሻ ላይ ጦር ያማዘዘው።

ነገር ግን ዛሬም ከታሪክ መማር አልተቻለም እናት ዛሬም የልጆቿን መርዶ ትረዳለች፣ ሕጻናት በየሜዳው ቀርተዋል ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን የሞት አፋፍ ላይ ናቸው። ዛሬም እልፍ አዕላፍ ሰዎች በከንቱ እየሞቱ ነው። ከዓመታት በኋላ ብዙ ሰማዕታትና ብዙ መታሰቢያ ሙዝየሞችንና ሃውልቶችን ለመገንባት የታቀደ ይመስላል።

ያለፈውን የዘነጋ ትውልድ፣ ጠባሳውን አላየሁም ብሎ የራሱን አዲስ ጠባሳ ለነገ ለማኖር የሚተጋ ትውልድ። አሁንም ቢሆን የተዘነጋው ሙዚየሙ አይመስልም፡፡ የተዘነጋው የያኔው ጠባሳ ነው። ባለቤት አልባው ሙዚየም ባለቤት አልባ ሞቶችን፣ ኃላፊነት የማይወሰድባቸውን ታሪካዊ ስህተቶችን ሊያስደግመን ይመስላል።

ትኩረት……. ትኩረት……. ትኩረት!

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here