ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል “ቼክ እና የሒሳብ ማንቀሳቀሻ ደረሰኞች ጠፍቶብናል” ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች የገንዘብ ዝውውር በጊዜያዊነት መታገዱን የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
ይህ የሆነው ዞንና ወረዳዎች የሒሳብ ማንቀሳቀሻ ደረሰኞች በመጥፋታቸው የገንዘብ እንቅስቃሴው ታግዶ ይቆይልን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሀሪ፤ “በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ‘ቼክ እና የሒሳብ ማንቀሳቀሻ ደረሰኞች ጠፍተውብናል፤ አጣርተን እስከምናሳውቃችሁ ድረስ የገንዘብ እንቅስቃሴ ታግዶ ይቆይልን፡፡’ ባሉት መሰረት እንዲታገድ ተደርጓል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህም በሰሜን ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች በሚገኙ በኹሉም ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች የገንዘብ ዝውውር እንዳይካሄድ ገደብ የተጣለ ሲሆን፤ ደብረታቦር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በኹሉም የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮችም ገንዘብ ዝውውር እንዳይኖር መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
እንዲሁም በማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን እና አዊ ብሔረሰብ ዞን በሚገኙ የተመረጡ ወረዳዎች ላይ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ተደርጓል ነው የተባለው።
“የገንዘብ እንቅስቃሴው እንዲታገድ የተደረገበት ዋና አላማው ደረሰኞች በመጥፋታቸው የሕዝብ ሃብት ያለአግባብ እንዳይባክን ታሰቦ እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለውም” ያሉት ኃላፊው፤ “ምንም እንኳ የገንዘብ እንቅስቃሴው እንዲታገድ ቢደረግም፤ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በግል የባንክ ቁጥራቸው አማካኝነት ስለሚገባላቸው ደመወዛቸው አይቋረጥም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፤ ኹኔታውን ዞኖች እያጣሩ መሆኑን በመግለጽ፤ ጠፍቷል ያሉትን ቼክ እና የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ደረሰኝ አግኝተው “የታገደው ገንዘብ ይለቀቅልን” የሚሉ ዞኖች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
“ገንዘቡ ይለቀቅልን ላሉት ዞንና ወረዳዎች እየለቀቅን በመሆኑ ያለተለቀቀላቸው ዞንና ወረዳዎችን ድጋሜ አጣርተን ማስተካከያ የምንጽፍ ይሆናል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው ቀጥሎ ይገለጻል ስላሉት ማስተካከያ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
ከቀናት በፊት ብሔራዊ ባንክ የክልሉ መንግሥት ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ገደብ ጥሎ እንደነበር ይታወሳል።



