በተሸከርካሪዎች ላይ የሚገጠም አውቶማቲክ የአደጋ ጠቋሚ መሳሪያ እና የጫማ ሶልን በኬሚካል የሚያጸዳ ማሽን ይፋ ተደረገ

0
304

ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአገራችን እየደረሰ ያለውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመከላከል እንዲያስችል ታስቦ፤ በተሸከርካሪ መኪኖች ላይ የሚገጠም አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሳሪያ እንዲሁም፤ ንጹህ የሆነ የሥራ እና የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ያስችላል የተባለለት የጫማን ሶል በኬሚካል የሚያጸዳ ማሽን መስራታቸውን የሥራ ፈጣራው ባለቤት የሆኑት ጎይቶም ገብረ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

ጎይቶም ገብረ ዮሐንስ ዛሬ ነሐሴ 25/2015 በመዲናዋ በሚገኘው ሀርመኒ ሆቴል በሰጡት መግለጫ፤ “በተሽከርካሪው ግራና ቀኝ ጎን እንዲገጠም ተደርጎ የተሰራ እና በዳሽ ቦርድ ላይ በተዘጋጀለት ቦታ ስናበራው አገልግሎቱን የሚጀምር ማሽን ሰርቼ ይፋ አድርጊያለሁ፡፡” ብለዋል፡፡አክለውም፤ መሳሪያው በቀይ ምልክት ቁም (Stop) የሚል ጹሁፍ ያለው የእጅ ምልክት የያዘ መብራት እና በማታ ወቅት አንጸባራቂ መብራት ያለው የቁም ምልክት ውዝዋዜን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ውዝዋዜን ሲፈጥር በቀኝ ደርቦ ለሚመጣው አሽከርካሪ ግልጽ ምልክት በመስጠት፤ “ፊት የሚሻገሩ እግረኞች፣ ተሽከርካሪዎች ወይም እንስሳቶች ስላሉ ፍጥነትን ቀንስ ከዛም አልፎ ቁም!” በማለት አደጋ እንዳይደርስ የሚያደርግ መሳሪያ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

“በቀኝ በኩል ደርቦ የመጣው ተሽከርካሪ በእኛ ቀኝ እስፖኪዮ መቆሙን ስናረጋግጥ፤ ከዳሽ ቦርድ ላይ ኦፍ ስናደርገው የቁም ምልክቱ በመጀመሪያው ቦታ ላይ ተመልሶ፤ በተሽከርካሪው አካል ላይ ውበቱን በጠበቀ መልኩ ልክ እንደ እስፖኪዮ ተለጥፎ ይቆማል” ሲሉ አክለዋል፡፡ በተሸከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው መሳሪያም ለስርቆት የሚጋለጥ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኹለተኛው የፈጠራ ሥራቸው የጫማን ሶል በኬሚካል የሚያጸዳ ማሽን መሆኑን የገለጹት ጎይቶም፤ በኹሉም ቦታ የሚያገለግል እና በተፈለገው መጠን እና ቅርጽ ሊሰራ የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ማሽኑ የራሱ የሆነ የኬሚካል መያዣ ታንከር ያለው ሲሆን፤ ከጫማ የሚጠረጉትንም ቆሻሻዎች መቀበያ ሳጥን ያለው፣ በማንኛውም የቤት ቆጣሪ የሚሰራ እና ብዙ ኃይል የማይፈጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “ለእጅ ማጸጃ (ሳኒታይዘር) ቦታ የተዘጋጀለት እንዲሁም በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚነዳ ጎማ የተገጠመለት ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የፈጠራ ሥራው ባለቤት ጎይቶም ገብረ ዮሐንስ በዚህ ሥራቸው በአእምሮአዊ ንብረት ባለስልጣን የባለቤትነት መብት ፍቃድ እንዳገኙ እና ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ብሎም ከአጋር ተቋማትም የድጋፍ ደብዳቤና እውቅናን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here