የኤርትራ ሠራዊት “አንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በአልጀርስ ስምምነት መሰረት የእኔ ናቸው” እያለ መሆኑ ተጠቆመ

0
426

ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

የኤርትራ ሠራዊት በአሁኑ ወቅት በምስራቃዊ ትግራይ ጉልማሃዳ ወረዳ፣ ሶቢያ ከተማ፣ ዛላአንበሳ፣ ገላ እንዲሁም እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁም፤ “እነዚህ አካባቢዎች “በአልጀርስ ስምምነት” መሰረት የእኔ ናቸው።” እያሉ መሆኑን ባይቶና ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የባይቶና ፓርቲ ሥራ አመራር ዮሴፍ በርሄ በእነዚህ ሥፍራዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት አልፎ አልፎም ቢሆን እንደሚንቀሳቀስ ጠቅሰው፤ የኤርትራ ወታደሮች በነዋሪው ላይ የከፋ በደል ሲያደርሱ ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ አልተስተዋለም ብለዋል፡፡

“ከአዲግራት ወደ ኢሮብ የሚወስደው መንገድ በኤርትራ ኃይሎች ተዘግቷል።” ያሉት ዮሴፍ በርሄ፤ “አሁን ላይ ወደዛ ለመሄድ አሲምባ እና ጉንዳጉንዲን የመሳሰሉ እጅግ ፈታኝ እና አድካሚ መንገዶችን መጠቀም ግድ ሆኗል።” ብለዋል፡፡

“እንዲህም ሆኖ ሕዝቡ አማራጭ ስለሌለው የሚደርስበትን ግፍ እና በደል ችሎ እየኖረ ነው።” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የኤርትራ ሠራዊት በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የጠቆሙት ዮሴፍ፤ የኤርትራ ኃይሎች በነዋሪው ላይ እያደረሰ ያለው አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን እና ነዋሪውን ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

አክለውም፣ አሁንም በፈለጉት ሰዓት ነዋሪውን ይገድላሉ፣ ሴቶችን ይደፍራሉ፣ አፍነው ይወስዳሉ ካሉ በኋላም፤ “ያሻቸውን ቢያደረጉ የሚያስቆማቸው አካል የለም።” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል ኢሮብ ከተማ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ታሕሳስ 29/2013 የኤርትራ ሠራዊት ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሆኑ ንጹሃንን መረሸኑን አስታውሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ የ20 ሰዎች አጽም ተቆፍሮ ወጥቶ መቀበሩን ነው የተናገሩት።

ንጹሃኑ ልዩ ሥሙም ህዳ ሞሳ እንዲሁም አዎ በሚባሉ ቦታዎች መገደላቸውን ያስታወሱት ዮሴፍ፤ የተገደሉት ሰዎች በወቅቱ በጅምላ መቀበራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውም አጽማቸውን አውጥተው በኃይማኖታዊ የመቃብር ሥፍራ ለማሳረፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሲማጸኑ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ባለፈው እሁድ  ነሐሴ 28/2015 በኢሮብ ከተማ ሀረዘ ቀበሌ 20 የሟቾች አጽም ወጥቶ እዳሞሳ በሚገኘው አቡነ መዝገቦ ቤተክርስቲያን፣ ሐረዛ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን እንዲሁም አዎ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን መቀበራቸውን ነው የተናገሩት።

አሁንም ከ30 በላይ የሚሆኑ ሟቾች አጽማቸው እንዳልወጣ እና የሟች ቤተሰቦች ጊዜያዊ አስተዳደሩን ፈቃድ በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ለኹለት ዓመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሲዋጉ እንደነበር የሚነግርላቸው የኤርትራ ኃይሎች፤ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ ግዛት መውጣት የነበረባቸው ቢሆንም እስካሁንም በክልሉ ብዙ ቦታዎች እንደሚንቀሳቀሱ ይገለጻል።

በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነት ማግስት ኹለቱን አገራት ለእርቅና መግባባት እንደሚያበቃ ግምት የተሰጠው ሰነድ በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ፣ ታህሳስ 03/1993 በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተፈርሟል።

ይህን ተከትሎም አምስት አባላት ያሉት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የራሱን ምርመራ አድርጎ፤ አለመግባባት የፈጠሩ የድንበር ቦታዎች ለየትኛው አገር እንደሚገቡ ለመወሰን እንዲችል በወቅቱ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here